ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የገፅታና የውበት አጠባበቅ እንዲሁም የጌጣ ጌጥ አጠቃቀምን በተመለከተ ከ5 እስከ 50 ሺሕ ብር እና ከባድ እርምጃን የሚያስቀጣው ደንብ ወደ ትግበራ መግባ፤ በሆቴሎች መካከል ወጥነት ያለው የአለባበስ ስርዓትን ለማምጣት መጥቀሙን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ለአሐዱ አስታውቋል።

ደንቡ ከሴቶች በተጨማሪ የወንዶች አለባበስንም ያካተተ መሆኑን የሚያነሱት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰሎሞን፤ በቀጥታ ሆቴሎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን አገልግሎቱ በሆቴሎች ውስጥም የሚሰጥ በመሆኑ ምንም እንኳን በማህበሩ ሥር በሚገኙ ሆቴሎች አስቀድሞም ችግሩ ጎልቶ የማይታይ ቢሆንም፤ በአሰራር ደረጃ ሁሉም ወጥነት ያለው አለባበስን እንዲከተል ለማድረግ ይጠቅማል ብለዋል።

ማህበሩ እንደ ሸራተን አዲስ፣ ማሪዮት እና ራዲሰን የመሳሰሉ ሆቴሎችን ጨምሮ ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ሆቴሎችን የያዘ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቷ፤ እነዚህ ሆቴሎችም በአብዛኞው የአለባበስ ስርዓትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መስፈርትን የሚከተሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት ደንቡ ከመውጣቱ በፊትም ከባህል ያፈነገጠ አለባበስን የሚከተሉ እንዳልነበሩ ገልጸዋል።

በእነዚህ ሆቴሎች ውስጥ በተለይም ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በሚደረጉበት ጊዜ በመንግሤት በኩል በሚቋቋም ኮሚቴ አማካኝነት ስለሚመጡት እንግዶች ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ፤ የአለባበስ ስርዓቱን ጨምሮ የሆቴሎች የመስተንግዶ ሁኔታ ክትትል እንደሚደረግበትም ተናግረዋል።

በዚህ አግባብ ግን ክፍተት ሲገኝ የማስተካከል ሥራ እንደሚሰራ ያነሱት ፕሬዝዳንቷ፤ ከማህበሩ ውጪ ያሉ ሆቴሎችና የሆቴል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሙሉ ደንቡን ያማከለ የአለባበስ ስርዓት ቢከተሉ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ኮሚሽን በፀደቀውና ተግባር ላይ እየዋለ በሚገኘው ደንብ መሰረት ያላስተካከሉ ተቋማት ላይ፤ ከግንዛቤ ፈጠራ ባሻገር የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በመስጠት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ አሐዱ ሬዲዮ መዘገቡ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ