ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለአንድ ተገልጋይ የመኖሪያ ፈቃድ ለማደስ 700 ሺሕ ብር የጠየቀበት የተገልጋይ ቅሬታ ምላሽ ማሰጠቱን አስታውቋል፡፡

ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የቀረቡለትን አቤቱታዎች መሰረት አድርጎ ባደረጋቸው ምርመራዎች ውጤት ያገኙትን ገልጿል።

Post image

ከአቤቱታዎቹ መካከል ከልማት ተነሽነት ጋር ተያይዞ የቀረቡ ቅሬታዎች እና የአስተዳደር በደል ይገኙበታል ተብሏል።

በዚህም የኢሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት ጋር ተያይዞ አንድ ባለጉዳይ በተከታታይ ለአምስት ዓመታት ሲያሳድሱት የቆዩትን የመኖሪያ ፈቃድ ለማደስ በዚህ ዓመት ሲስተም በመቋረጡ ስላልተደረገ ክፍያ መጠየቃቸውን ተቋሙ ገልጿል።

በዚህም አምስት ሺሕ ዶላር ወይንም 700 ሺሕ 382 ብር መጠየቃቸውና የአስተዳደር በደል መፈጸሙን አንስቷል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያለ አግባብ እንዲከፈል የተጠየቀው ገንዘብ ቀሪ ተደርጎ ሕጉ በሚጠይቀው አግባብ መሰረት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቋል።

በተመሳሳይም በተለያዩ ሁለት አካባቢዎች ከልማት ተነሸነት ጋር በቀረቡ 12 አቤቱታዎች ምርመራ ተደርጎባቸው ለ11 የካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው መደረጉን እና ለአንድ ቅሬታ አቅራቢ ምትክ እንዲሰጥ መደረጉን ጠቁሟል።

እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ ውሃ ፍሳሽ አገልግሎት ሠራተኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሕዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተፈቀደው የደመወዝ ጭማሪ፤ 'የበጀት እጥረት አለ' በሚል እስከ ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ሳይከፈላቸው መቆየቱን በማረጋገጥ የደመወዝ ማስተካከያ ተደርጎላቸው ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉትን ተቋሙ ገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ