ሕዳር 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት የሚያስገቧቸው መሣሪያዎች ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ ገንዘብ ሚኒስቴር መፍቀዱ ተገልጿል።
የቀረጥ ነፃ መብቱ የተፈቀደው የገንዘብ ሚኒስቴር አዲስ ባወጣው መመሪያ ሲሆን፤ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ያሉ ወይም ለኅብረሰሰቡ ነፃ አገልግሎት ለሚሰጡ የትምህርት ተቋማት፣ ለጤና ተቋማት፣ ለሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ የአዕምሮ ሕመምተኞችና የአካል ጉዳተኞች መርጃ ድርጅቶች ከውጭአገር በዕርዳታ የሚላኩ ዕቃዎች ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ ሆነዋል፡፡
በተጨማሪም፣ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረስባቸው ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ለሚሰጡ ድርጅቶች ከውጭ ሀገር በዕርዳታ የሚላኩ ዕቃዎች ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ ተደርዋል።
እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ተቋሞች፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር በሕግ በተፈቀደው መሠረት ወደ ሀገር የሚያስገቧቸዉ የመከላከያና የሕዝብ ደኅንነት መሣሪያዎች፣ ለነዚሁ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችናና አክሰሰሪዎችም በተመሳሳይ ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ መወሰኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከቀረጥና ታክስ ነፃ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ የተፈቀዱ ዕቃዎች እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ ወደ አገር የሚገቡ ሳንቲሞች፣ የገንዘብ ኖቶች እንዲሁም የብርና የወርቅ ጠገራዎች በተመሳሳይ ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ ተደርገዋል።
ለኅብረተሰቡ በነፃ የሚሰጡ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እንዲሁም፤ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት ከውጭ አገር በዕርዳታ የሚላኩ ዕቃዎች ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ መደረጋቸውን መመሪያው ያመለክታል።
በመመሪያው መሠረት ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱት ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ ሆነው ሊገቡ የሚችሉት፤ ዕቃዎቹ በዕርዳታ የተገኙ መሆኑን የሚያረጋግጥ የዕርዳታ የምስክር ወረቀት ሲቀርብ ነው ተብሏል፡፡
ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ ቢፈቀድም፤ ይህንን መሠረት በማድረግ ያልተገባ ጥቅም የመሰብሰብ ድርጊት እንዳይፈጠር የተወሰኑ ዕቃዎች የቀረጥ ነፃ መብቱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ክልከላ ጥሏል።
ክልከላ የተጣለባቸው ዕቃዎች ተብለው በመመሪያው የተጠቀሱት፣ ከስምንት መቀመጫ በታች ያላቸው አውቶሞቢሎችና የእነዚህ መለዋወጫዎች፣ ባለአንድ ወይም ባለሁለት ጋቢና ፒካፕና የእነዚህ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫዎች እንዲሁም ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችና መሣሪያዎች እንደሆኑ ዘገባው አመላክቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ተፈቀደ
የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት የሚያስገቧቸው መሣሪያዎችም ከቀረጥ ነፃ ሆነዋል