ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን የሚችሉበትን አዋጅ አጽድቋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም የመሬት ባለይዞታ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው የአዋጅ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ከዚህ ቀደም የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ ስያሜ፤ "የውጭ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት አዋጅ" ወደሚል ተቀይሮ እንዲጸድቅ በአራት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ አስተላልፏል።
አዋጁ በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ፣ የሪል እስቴት ዘርፉን ለማነቃቃት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር እና ሌሎች ጥቅሞች እንዳሉት ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ ይህ አዋጅ ከመዘጋጀቱ በፊት፤ የውጭ ዜጎች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከሌላቸው በቀር የንብረት ባለቤት እንዳይሆኑ የሚከለክል አሰራር ስትከተል ቆይታለች።
ይህ አዋጅ መጽደቁ በኢትዮጵያ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ሚዛን ለማስጠበቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፤ የቤት ልማት እና ተደራሽነትን "ይበልጥ ለማነቃቃት" የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመሬት እና የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅደው አዋጅ ጸደቀ
