ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ ሪል ስቴት የቤት ግንባታ ዘርፍ ላይ መሳተፋቸው ውድድርን ከመፍጠሩ በተጨማሪ፤ በዘርፉ ያለውን የአስተዳደር ክፍተት እንደሚፈታ የሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር ለአሐዱ ገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ፤ "የውጭ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት አዋጅ" በሚል ተቀይሮ እንዲጸድቅ በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ አስተላልፏል።

"አወጁ መጽደቁ የውጪ ሀገር ባለሀብቶች በቤት ግንባታው ዘርፍ መሳተፋቸው የተሻለ ፋይናንስ ወደ ሀገር ውስጥ ይዘው እንዲሚመጡ ያደርጋቸዋል" ያሉት የሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር ፕሬዝንደንት አቶ አለማየሁ ከተማ፤ በተጨማሪም አሁን ላይ በዘርፉ የሚስተዋለውን የአስተዳደር ችግር ለመፍታት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ለአሐዱ ገልጸዋል።

"ባለሃብቶቹ ወደ ሀገር ውስጥ መምጣታቸውን እና በሪል እስቴት የቤት ግንባታ ዘርፍ ላይ መሰማራታቸውን በአውንታዊ መንገድ መመልክት ይገባል" ያሉም ሲሆን፤ ይዘውት የሚመጡትን ልምድ እና እውቀት ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አክለውም ባለሀብቶቹ በዘርፉ መሳተፋቸው እንደ ሀገር ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ "በዘርፉ ላይ የተሰማሩ የሪል እስቴት የቤት አልሚዎች ተፎካካሪ እንዲሆኑም ያስችላል" ብለዋል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ሄለን ደበበ በበኩላቸው፤ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሪል እስቴት የቤት ግንባታ ላይ መሳተፋቸውን የሚኖረውን አስተዋጽዖ በተመለከተ ጥናት መደረጉን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዘርፉ ላይ የፋይናንስ እጥረት እንዳለ መመላከቱን አንስተው፤ ይህም በሀገር ውስጥ በቤት ግንባታ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ግንባታው የተራዘመ ጊዜ እንዲወስድ እና የቤት ዋጋ እንዲንር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ፤ የራሳቸውን ፋይናንስ ይዘውን እንደሚመጡ እና በቤት ግንባታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የዋጋ ንረትን እንደማያስከትልም አስረድተዋል፡፡

አክለውም "የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ገንብቶ አለማጠናቀን እና በግንባታ መራዘም ምክንያት ዋጋ እንዳይንር ያግዛል" ብለዋል፡፡ እንዲሁም የውጭ ባለሃብቶች በሀገር ውስጥ በሪል ስቴት የቤት ግንባታ ላይ መሳተፋቸው የቴክኖሊጂ ሽግሽግ እንዲኖር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ