መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚኒስቴሩ እውቅና ውጪ እየሰሩ ባሉ አስጎብኚዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ቱሪዝም ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
እርምጃው ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ልታገኝ የሚገባትን ገቢ ለማስጠበቅ እና የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር ያለመ ነው ተብሏል።
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው፤ ከሚኒስቴሩ ኃላፊነቶች መካከል ለአስጎብኚ ተቋማት እና ግለሰቦች ፍቃድ የመስጠትና የማደስ ሥራ አንዱ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፉ አስጎብኚነትን ጨምሮ በሌሎች ከቱሪዝም ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች የሚጠበቅባቸውን አሟልተው፣ በዘርፉ ለመሰማራት የሚያስፈልጋቸውን ሕጋዊ እውቅና ሳያገኙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሆኑ፤ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ሥራ አስፈጻሚው አክለውም፤ ያልተፈቀደ አገልግሎት በሚሰጡ አስጎብኚዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደየጥፋቱ ደረጃ እንደሚለያይ ገልጸው፤ የቅጣት አፈጻጸሙ በቅርብ ጊዜ ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው መመሪያ መሠረት እንደሚሆን አስረድተዋል።
ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የቱሪዝም ዘርፉን በማዘመን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ጎብኚዎች የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ላይ አተኩሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝም የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን ከሕገ-ወጥ አሠራር መከላከል እና የጎብኚዎችን የአገልግሎት ምቾት ማረጋገጥ፤ የዚህ እርምጃ አካል ነው ተብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ