ጥቅምት 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ትኩረት ተሰጥቶት በድርድር እንዲፈታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሳስበዋል።
ችግሩን በሐይማኖት አባቶች እና በሽማግሌዎች ብቻ ለመፍታት ከመጣር ይልቅ፣ በድርድር እና በእውነተኛ አካታች ውይይት መፍታት እንደሚገባም የፓርቲዎቹ አመራሮች ለአሐዱ ተናግረዋል።
የአንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሲሳይ ደጉ፤ "መንግሥት እና አማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች ዋናው ሀገራዊ ምክክር ከመካሄዱ በፊት ያለው የጸጥታ ችግር በሰላም መፈታት አለባቸው" ብለዋል።
አቶ ሲሳይ የፌዴራል መንግሥት "ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጥሪ አቅርቤያለሁ" የሚለውን ቃሉን ተግባራዊ እንዲያደርግ፤ ጥረት እየተደረገ ከሆነም መንግሥት ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ የፋይናንስ ንብረት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ሐድጉ በበኩላቸው፤ "መንግሥት በአማራ ክልል ያለውን ችግር ለፍታት ከድርድር ይልቅ በማኅበራዊ እና ሐይማኖታዊ መንገዶችን መጠቀሙ ተገቢ አይአለም" ብለዋል።
በክልሉ እየተካሔደ ያለውን የታጣቂ ኃይሎች ግጭት "የጋራ አስታራቂ በመምረጥ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል" ብለዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታጠቅ አሰፉ በበኩላቸው፤ "በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር እንዲፈታ እውነተኛ እና በሁሉም ወገኖች የሚታመን ውይይት መደረግ አለበት" የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።
"በክልሉ ያለው ችግር በመሸፋፈን የሚፈታ አይደለም" ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የመንግሥት በሆደ ሰፊነት የማሕብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
"እውነተኛና ሁሉን ያካተተ ድርድር ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው" ሲሉም አጽንኦት ሰጥተውበታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የክልሉ የጸጥታ ችግር በድርድር እንዲፈታ ፓርቲዎች አሳሰቡ