ጥቅምት 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በተያዘው የ2018 ሩብ ዓመት 5 ሺሕ 968 በሚሆኑ የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መዉሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

ከእነዚህም መካከል 1 ሺሕ 44ቱ የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ የንግድ ፈቃዳቸው መሰረዙን የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ለአሐዱ ተናግረዋል።

Post image

ቀሪዎቹ የንግድ ድርጅቶች ማለትም፤ 4 ሺሕ 924 የሚሆኑት ደግሞ፤ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸውና የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸው፤ በምህረት ወደ ቀደመ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በእነዚህ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደው፤ ሕጋዊ የሆነ የንግድ ፍቃድ ባለመያዛቸው ወይም የያዙትን የንግድ ፍቃድ ሳያሳድሱ በመቀጠላቸዉ፣ የንግድ ፍቃዳቸውንና የምርታቸውን የዋጋ ተመን በሚሰሩበት ተቋም በር ላይ ባለመለጠፋቸዉ እንዲሁም ምርትን ከማህበረሰቡ ሲደብቁ በመገኘታቸው ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ ከ700 ሺሕ በላይ የንግድ ድርጅቶች ሕጋዊ የንግድ ፍቃድ ወስደው በዘርፉ መሰማራታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በአጠቃላይ በተያዘው ሩብ ዓመት ሕጋዊ ባልሆነ የንግድ ተሳትፎ ሲሰሩ በተገኙ ተቋማት በተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ፤ 276 ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።

"ቢሮው በየትኛውም የንግድ ተቋም ላይ ሳያጣራ ምንም አይነት አስተዳደራዊ እርምጃ አይወስድም" ያሉም ሲሆን፤ ነገር ግን ሕጋዊ ባልሆኑ የንግድ አሰራሮች ላይ ሲሳተፍ የተገኘ ማንኛውም ተቋም ሆነ ግለሰብ ከሕግ ማምለጥ አይችልም ብለዋል።

አክለውም "የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ዋናኛ አላማው ድርጅቶች እንዲበዙ የድጋፍ አገልግሎት መስጠት ነው እንጂ መቅጣት አይፈልግም፤ እናም የንግድ ድርጅቶች አዋጭውና አትራፊውን ሕጋዊ የንግድ አሰራር መከተል ይገባቸዋል" ሲሉ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ