ጥቅምት 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ አብዛኞቹ ቅሬታዎች መካከል ዋነኛው፤ "ዳኛ ይነሳልኝ" የሚለው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ለአሐዱ አስታውቋል።

ተገልጋይ ዳኛውን ለማስነሳት ጥያቄ ቢያቀርብም፤ ዳኛው ጉዳዩ በሕግ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላ የማይነሳበት ሁኔታ ስለመኖሩም ተገልጿል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዳኝነት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዳኛ ዳንኤል አበበ፤ "በፍርድ ቤቱ የሚበዙት ቅሬታዎች ዳኞች እንዲቀየርላቸው የሚጠይቁ ቢሆንም፤ አሰራሩ ቅሬታ የቀረበበት ዳኛ እንዲቀበል ወይም እንዲከለክል እድል ይሰጠዋል" ብለዋል።

Post image

ዳኛው ለመነሳት ፍቃደኛ ካልሆነ፣ ጉዳዩ ከጎኑ ባለ ዳኛ ታይቶ የመጨረሻው "ይነሳ" ወይም "አይነሳ" ውሳኔ እንደሚሰጥ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ "እኛ ዳኛ ማንሳት አንችልም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እንዲሁም "እግድ ይሰጥልኝ" እና "እግድ ይነሳልኝ" የሚሉ፤ ከጊዜያዊ ትዕዛዞች ጋር የተያያዙ ያላቸው ቅሬታዎች ከፍተኛ ቁጥር እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም "በሂደቱ በእኩልነት አልተሰማሁም"፣ "በችሎት ተመናጭቄአለሁ" እና "ሀሳቤን አይሰሙም" የሚሉ ቅሬታዎችም ይበዛሉ ብለዋል።

እንደከዚህ ቀደሙ በርከት ያሉ ባይሆኑም፤ አልፎ አልፎ "ከዳኞች ገንዘብ እንጠየቃለን" የሚሉ ሐሳቦች እንደሚነሱም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት ያስቀመጠውን ዕቅድ መቶ በመቶ ማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

የዳኞችና የፍርድ ቤት ሠራተኞች ሥነ-ምግባር ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ፍርድ ቤቱ አጽንዖት ሰጥቷል።

በተጨማሪም፤ የዳኛን ትዕዛዝ የማያከብሩ አካላት፣ በተለይም በክፍለ ከተማና በሌሎች የመንግሥት አስፈጻሚዎች ላይ እስከ እስር የሚደርስ ውሳኔ እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ