ጥቅምት 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና በጤና ሚኒስቴር በጋራ ስምምነት በማድረግ በክልሉ የማይሰጡ የሕክምና አገልግሎቶችን አዲስ አበባ በሚገኙ 6 ሆስፒታሎች እንዲሰጥ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የክልሉ የጤና መድኅን ተገልጋዮች አገልግሎቱን ከሚያገኙባቸው ሆስፒታሎች መካከል፤ ጥቁር አንበሳ፣ ጳውሎስ እና የካቲት 12 ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ይገኙበታል ብሏል፡፡

የቢሮው የሃብት አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አበባው አገልግሎቱ ከክልሉ ሆስፒታሎች አቅም በላይ ሆነው በሪፈር ወደ አዲስ አበባ ለተላኩ ታካሚዎች ብቻ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ ከሆስፒታሎች በተጨማሪ ከነማ ፋርማሲዎችም የስምምነቱ አካል መሆናቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image

“ስምምነቱ በክልሉ ጤና መድኅን የታቀፉ ታካሚዎች እንደ ካንሰር እና ኩላሊት ባሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎች ምክንያት በፊረር አዲስ አበባ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ቢላኩ ከተጨማሪ ወጪ የሚታደጋቸው ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የሃብት አሰባሰብ ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ በ2017/2018 የበጀት ዓመት ከአባላት የተሰበሰበው የክልሉ የጤና መድኅን መዋጮ ከመንግሥት ድጎማ ጋር 5 ቢልዮን መድረሱ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት መክፈል ለማይችሉ ዝቅተኛ ገቢ የጤና መድኅን ተጠቃሚዎች የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

81 ከመቶ የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች መካከለኛ እና ከፍተኛ በሚሉ ሁለት ምድቦች በጤና መድኅን አባልነት ተመዝግበው እና የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ መዋጮ ከፍለው አገልግሎት በማግኘት ላይ እንደሆኑም አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

በአገልግሎቱ ላይ የሚቀርቡትን ቅሬታዎች ለማሻሻል ወጥ አሠራር ተዘርግቶ በ1 ቢልዮን ብር ወጪ ለደብረማርቆስ፣ ለደሴ፣ ለደብረ ብርሃን የሪፈራል ሆስፒታሎች የሕክምና ቁሳቁሶች ለማሟላት እቅድ ተይዟል ተብሏል፡፡

ቢሮው ለ2018/2019 የበጀት ዓመት የአባላትን ተሳትፎ ከ81 ከመቶ ከፍ ለማድረግ፤ የአባልነት የገንዘብ ክፍያ መጠንንም 7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየሠራ እንደሆነም ዳይሬክተሩ አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ