ጥቅምት 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርት ለማስገባት በቀን ከ4 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ወር ወረፋ እንደሚጠብቁ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኮነን (ዶ/ር) ይህን ችግር የሚያስቀር አሰራር እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በነዳጅ ኩባንያዎች አቅርቦትና ሥርጭት ዙሪያ በተደረገ ጥናት ላይ 'የተመሰረተ የገበያ ድርሻ ቀመርና የአሰራር ሥርዓት' ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የገበያ ድርሻ አሰራር ሥርዓት መሠረት ነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ለየትኛው ማደያ እንደሚጪኑ ፕሮግራም እንደሚወጣና፤ የኩባንያዎችን ፕሮግራም መሠረት በማድረግ 'የነዳጅ አቅራቢያ ድርጅት የጭነት ፕሮግራም' እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡

ወደ ጂቡቲ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች በሚወጣላቸው ፕሮግራም መሠረት እንዲሄዱ መደረጉ፤ አሽከርካሪዎች የሚያወጡትን ወጭ እና እንግልት እንዲሁም ኩባንያዎች የሚያወጡትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር እንደሚሆንም አመላክተዋል።

በተጨማሪም የሚገመት የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር፣ በሁሉም አካባቢዎች እኩል ተደራሽ እንዲሆንና በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ከጂቡቲ ጀምሮ የነዳጅ ሥርጭቱን ለመከታተል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

ይህም አሰራር የነዳጅ አቅርቦት እንዲሻሻል፣ ለሕብረተሰቡ የሚቀርበው የነዳጅ መጠን ፍትሃዊ እንዲሆን እንዲሁም፤ ለኮንትሮባንድ ተጋላጭ የሆኑ ድንበር አካባቢ የሚገኙ አካባቢዎች ላይ ኮታን መሰረት ያደረገ አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉንም ኩባንያዎች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሰራሩ በዚህ ሳምንት ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ