ጥቅምት 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ብድር ወስደው ወደ ሥራ ከገቡ 150 ፕሮጀክቶች ውስጥ 28 የሚሆኑት በባንክ ዕዳ ምክንያት በሀራጅ ጨረታ ተሸጠዋል ሲል የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለአሐዱ ገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ (ዶ/ር)፤ ከዚህ በፊት በክልሉ የእርሻ ልማት ሥራ ላይ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ከባንክ ብድር ወስደው ወደ ሥራ የገቡ 150 ባለሃብቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህ ውስጥ ዕዳቸውን መክፈል ያልቻሉ እና ሥራቸውን ትተው የወጡ የ28 ባለሃብቶች መሬት ከነፕሮጀክቶታቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሃራጅ ጨረታ እንደሸጣቸው ተናግረዋል፡፡
22 የሚሆኑት ደግሞ ዕዳቸውን እየከፈሉ ሥራ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ሌሎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ በክርክር ላይ የሚገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል በስፋት የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሳተፉ ባለሃብቶች ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ከክልሉ ወጥተው የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግን ሙዓለ ንዋያቸውን በክልሉ ፈሰስ ለማድረግ የሚገቡ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት 3 ወራት ፈቃድ ለመስጠት ከታሰበው 76 ባለሃብቶች ውስጥ 55 ለሚሆኑት ፈቃድ መሰጠቱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
አክለውም በክልሉ የአገልግሎት ዘርፉ ላይ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ቁጥር ዝቅተኛ ነው ያሉ ሲሆን፤ በተለይም በሆቴል እና ሪዞርት ዘርፉ ያለው የገበያ ዕድል ሰፊ ቢሆንም ብዙ ባለሃብቶች እየተሳተፉ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የወርቅ ማዕድን የማውጣት እርሻ እና ሌሎችም ኢንቨስትመንቶች ላይ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ዘርፉ ላይ ፈሰስ እንዲያደርጉ በኮሚሽን መስሪያ ቤቱ በኩል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
"መንግሥት የራሱን ድርሻ ይወጣል" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በአምራች ኢንደስትሪ ዘርፎች ላይ መስራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተው መስራት ይችላሉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጋምቤላ ክልል 28 ፕሮጀክቶች በባንክ ዕዳ ምክንያት በሀራጅ ጨረታ ተሸጠዋል ተባለ