ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሰለሞን አሰፋ (ዶ/ር) በ59 ዓመታቸው ባጋጠማቸው የልብ ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ዶ/ር ሰለሞን የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ጊዜ እውቀታቸውን የሰጡ፣ ብዙዎችን ከሞት የሚታደገው የዲያሌሲስ ማሽን በበቂው እንዲገባ እና አቅም የሌላቸው ሰዎች እጥበቱን የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ነበሩ፡፡
ዶክተር ሰለሞን አሰፋ ከአባታቸው ከአቶ አሰፋ ከበደ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አይናለም ገ/ሥላሴ በመጋቢት ወር 1959 ዓ. ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቂርቆስ የሚባል አካባቢ ተወለዱ፡፡
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በፈለገዮርዳኖስ ት/ቤት የተማሩ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አብዮት ቅርስ ከፍተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል።
የከፍተኛ ትምህርታቸውንም በሕክምና ዘርፍ ከጎንደር ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዲግሪ፣ በማኔጅመንት እና በሕዝብ አስተዳደር ደግሞ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ማስትሬታቸውንም ሕንድ ሀገር ከሚገኘው ከ"ሲኪም ማኒፖል ዩንቨርሲቲ" በማዕረግ ተመርቀዋል፡፡

በተጨማሪም በሄልዝ ኬር ሰርቪስ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ዶ/ር ሰለሞን፤ በአስመራ የቁስለኞች ማዕከል በዳይሬክተርነት አገልግለዋል።
እንዲሁም በዲላ ሆስፒታል ከፍተኛ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በወረዳ 18 ጤና ጣቢያ በተለያዩ ኃላፊነት በዞን 3 ጤና መምሪያ የጤና አገልግሎት የቡድን መሪ ነበሩ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና ቢሮ የስልጠና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉም ሲሆን፤ በእንግሊዙ ሜዲካል ኢመርጀንሲ ሪሊፍ ኢንተርናሽናል በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ የፐብሊክ ሄልዝ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።
በተጨማሪም በ"ሚሊኒየም ኮሚኒቲ ቤዝድ አሶሴሽን በጎ አድጎት ድርጅት" ውስጥ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሰሩት ዶ/ር ሰለሞን፤ በአሜሪካ ኢንተር ሄልዝ ኢንተርናሽናል የክልል ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል።
እንዲሁም በሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል የምዕራብ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሰሩ ሲሆን፤ ከ2008 በኋላ ደግሞ የኩላሊት ሕመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ዶ/ር ሰለሞን ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የደም ባንክ ውስጥ ሠብሳቢ ሲሆኑ የሲስተር ሠልፍ ሄልዝ የቦርድ ሠብሳቢም ናቸው።
ከዚህ ባለፈ የኩላሊት ሕመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ለኩላሊት ሕሙማን በ8582 ላይ A ብለው ድጋፍ እንዲደረግ ያስተባብሩ፣ በሚኒሊክ በጳውሎስ እና በዘውዲቱ ሆስፒታሎች ውስጥ ዲያሊስስ በነፃ እንዲሠጥ ያደረጉ ትልቅ የሀገር ባለውለታ ነበሩ።
ዶክተር ሰለሞን አሰፋ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አፀደ አማረ ጋር በጋብቻ ከተሳሰሩ በኋላ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆችም አባት እንደነበሩ አሐዱ ራዲዮ ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመክታል።
ዶክተር ሰለሞን የኢትዮጵያ ኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በሰሩባቸው ዓመታት፤ የኩላሊት ህሙማን የሚደርስባቸውን የፋይናንስ ጫና ለማቃለል የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን የሰሩ ሲሆን፤ አቅም የሌላቸው ሰዎች እጥበቱን የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ዶክተር ሰለሞን አሠፋ በአጋጠማቸው የልብ ሕመም ምክንያት ትናንት ጥቅምት 30 ቀን 2017 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም ዛሬ ሕዳር 1 ቀን 2018 ከቀኑ 9 ሠዓት ላይ በቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም አሐዱ ከዶ/ር ሰለሞን የቅርብ ከቤተሰቦች ለማወቅ ችሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ