ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላቸውን ልዩነት በድርድር እንዲፈቱ እና በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና ለማሳደር እንደሚሰሩ አሐዱ ያነጋገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

"ሁለቱም ወገኖች የመደራደር ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም፤ እስከ አሁን ፍሬያማ ሙከራ አልታየም" የሚሉት የምክር ቤት አባላቱ፤ "በክልሉ የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ፣ እውነተኛ እና ሁሉን አሳታፊ ድርድር እንዲካሄድና ወጥቶ የመግባት ነጻነት እንዲከበር እንሰራለን" ብለዋል።

Post image

"ድርድር መተማመን ይፈልጋል" የሚል ሐሳብ የሰጡት የምክር ቤቱ የአማካሪ ኮሚቴ አባል አበባው ደሳለው (ዶ/ር)፤ የመደራደር ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹ ታጣቂዎች እምነት እንደሌላቸው መግለጻቸው አንዱ እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል። ስለሆነም "እውነተኛ እና ፍሬያማ ድርድር በሁለቱ ወገኖች መካከል እንዲካሄድ እንጥራለን" ብለዋል።

ሌላኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ገነነ ገደቡ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ታጣቂዎች ወደ ድርድር ጠረጴዛ አምርተው ጥያቄያቸውን በንግግር እንዲፈቱ "የሚጠበቅብኝን ሁሉ አደርጋለሁ" ብለዋል።

"ከክልሉ ሰላም እና እድገት ተጠቃሚ የማይሆን የማኅበረሰብ ክፍል አይኖርም” ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ ፌደራል መንግሥትም ሆነ ታጣቂዎች ለሰላም ያላቸውን ፈቃደኝነት እና ለሕዝቡ ያላቸውን አሳቢነት ለድርድር በመተባበር፣ ተኩስ በማቆም እና ወጥቶ የመግባት ነጻነት እንዲተገበር የድርሻን በመወጣት እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ በሰላም እጦት ምክንያት ለከፋ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች እየተጋለጠ እንደሆነ ያነሱት የምክር ቤት አባላቱ፤ በክልሉ ያለው "ቀውስ" ወደተረጋጋ ሁኔታ እንዲመለስ ሁሉም ወገን መተባበር እና መረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የተራዘመ ግጭት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ኪሳራው የከፋ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ስለ ችግሩ ከማውራት ይልቅ ስለ መፍትሔው መነጋገር የበለጠ እንደሚጠቅም አስምረውበታል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነውን የጎንደር አቢያተ መንግሥታት እድሳት በመረቁበት ወቅት በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ጊዜ አታባክኑ ወደ ድርድር ተመለሱ" ማለታቸው ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ