ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 14ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ (ኢትዮፔክስ)፣ 10ኛው የአፍሪካ እንስሳት አውደ ርዕይና ጉባኤ (ኤሌክ) እንዲሁም 5ኛው የአፒካልቸር እና አኳካልቸር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የባዮ ኢነርጂ የንግድ ትርኢት ጨምሮ ጥራት ያላቸው የዘርፉ ዋና አንቀሳቃሾች የሚሳተፉበት ይህ የእንስሳት ሃብት ልማት እና የተዋፅኦ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ርዕይና ጉባዔ ከጥቅምት 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው፡፡

በአውደ ርዕይ እና ጉባኤው ላይ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ተዋናዮች፣ የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላትና የቴክኖሎጂ እና ግብዓት አቅራቢዎች እንደሚሳተፉበት ተነግሯል፡፡

በእንስሳት መስኖ፣ በእንስሳት ጤና፣ በዶሮ እርባታ፣ በስጋና እንቁላል እንዲሁም በንብ እና በአሳ ሃብት ልማት ዘርፎች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የኹነቱ አዘጋጆች በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

Post image

በመግለጫውም በተዘጋጀው መድረክ ላይ የኢትዮ ዶሮ ኤክስፖ እንዲሁም የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት አውደ ርዕይ እና ጉባኤ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በኢትዮየዶሮ እርባትና በእንስሳት ሃብት ዘርፉ ላይ የተሰሩ ሥራዎች በልማት ቱሩፍቱ የተገኙ ውጤቶች አመርቂ ናቸዉ ተብሏል።

የጉባኤው አላማም ለዘርፉ ባለሙያዎችና ለንግዱ ማህበረሰብ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ፣ የእውቀት ሽግግር ማምጣት እንዲሁም፤ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ በልማት ዘርፉ ላይ ያለውን አስተዋፅኦ ማሳደግ ነው ሲሉ የፕራና ኢቨንት የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሜሮን ሰሎሞን ተናግረዋል።

በኢትዮጵ ባህላዊ የዶሮ እስካሁንም በስፋት የተለመደ ነው ያሉት የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጇ፤ ነገር ግን ዘርፉን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት ስትወዳደር ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ባለቤት ብትሆንም፤ በዘርፉ እያሳየች ያለው ምርታማነት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ዓውደ ርዕይና ጉባኤ ላይ አጠቃላይ መሰረታቸውን በኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ቼክሪፐብሊክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ታንዛኒያ፣ ግብጽ፣ ጣሊያን፣ ብራዚል፣ ኬኒያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ቱርክ እና ሶሪያ ያደረጉ ዓለም አቀፍ የዘርፉ መሪዎች እና ጠንካራ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚገኙ ተነግሯል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ