ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እያካሄደ ባለው የ23ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ ከማህበሩ ጋር በጋራ በመስራት እና ታዓማኒ የሆኑ መረጃዎችን በማጋራት የመምህራን ችግሮች እንዲፈቱ ላደረገው አስተዋፅኦ አሐዱ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የእውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 23ኛ መደበኛ ጉባኤ ''ለትምህርት ስርዓታችን ተጠያቂነት የድርሻችንን እንወጣለን'' በሚል መሪ ሀሳብ 23ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚህም ጉባኤ ላይ አሐዱ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የማህበሩን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት፣ በትምህርት ሥራ ላይ የድርሻውን ለመወጣት የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንዲሁም ማህበሩ በሀገራዊ ጉዳይ የሚያራምደውን አቋም በሚዛናዊነት ተከታትሎ በመዘገብና ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ከማህበሩ ጋር ለሚሰራቸው ሥራዎች የእውቅና ምስክር ወረቀት መስጠቱን ማህበሩ ገልጿል።
የማህበሩ 23ኛ መደበኛ ጉባኤ ከጥቅምት 4 እስከ 6 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና በአዳማ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ማህበሩ በዛሬው ጉባኤው የሥራ አስፈፃሚዎችን ምርጫ ማድረግ እና የማህበሩን አሰራሮች ለማሻሻል ያወጣውን መመሪያ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባኤው ላይ "ቅድሚያ ለትምህርት" በሚል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር እንደሚኖር የገለጹት የማህበሩ ፕሬዝደንት ዮሀንስ በንቲ (ዶ/ር)፤ የትምህርት ዘርፉ ላይ ገንዘብ ማውጣት ወጭ ሳይሆን መዋለ ንዋይን መጀመር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሁሴን በጉባኤው ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ "እንደ ሀገር የሚጠበቁብን ጉዳዮች ሰፊ ናቸው። ደሞክራሲን በትክክል መለማመድ አለመቻላችን ለግጭት ዳርጎናል" ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ ደግሞ መምህራንን፣ ተማሪዎችን እና ትምህርት ቤቶችን እያሳጣን ነው ያሉት አቶ አህመድ፤ ለዚህ ደግሞ መምህራን አገናዛቢ ዜጋን የመፍጠር ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በ1940 ዓ.ም የተመሠረተው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በአሁኑ ሰዓት 729 ሺሕ አባላትን በውስጡ ይዟል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ