ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በቀዳሚነት ከተመሰረቱት የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ፤ በመላው ዓለም የክፍያ አገልግሎት በመስጠት ስመጥር ከሆነው ቪዛ ኢንኮርፖሬትድ ጋር ባንኩ እየሰጠ ያለውን ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርድ አገልግሎት ለማስፋፋት እና ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል የአምስት ዓመት የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የአጋርነት ስምምነቱ ወጋገን ባንክ ለደንበኞቹ በሚያሰራጨው የወጋገን ቪዛ ዓለም አቀፍ ክፍያ ካርድ ብዛት እና ደንበኞቹ በካርዱ በሚያንቀሳቅሱት የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ተመስርቶ ከቪዛ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ድጋፎችን ማለትም፤ የሠራተኞች ስልጠና፣ የተሻሻሉ ሶፍትዌሮችን ተጠቃሚ መሆን እና ሌሎች አገልግሎቱን እንዲሁም የውስጥ አሰራሩን የሚያዘምኑ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ማግኘት ያስችለዋል ተብሏል፡፡

Post image

በተጨማሪም ወጋገን ባንክ የቪዛን የስጋት አስተዳደር እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ዘመናዊ የትክክለኝነት ማረጋገጫ ስርዓት በመጠቀም ሁሉም የካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

በወጋገን ባንክ በኩል የአጋርነት ስምምነቱን የፈረሙት የባንኪንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ኪዳነ ገ/ሥላሴ የትብብር ስምምነቱ ወጋገን ባንክ አስተማማኝ፣ ዘመኑን የዋጀ እና ለደንበኞቹ ከዓለም አቀፍ የባንክ ስርዓት ጋር የተሳሰረ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ከማሳደግ አንፃር ትልቅ እመርታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የአጋርነት ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ወደላቀ ደረጃ በማድረስ ወጋገን ባንክ በፍጥነት እያደገ በሚገኘው የኢትዮጵያ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ስርዓት ውስጥ የራሱን ጉልህ አስተዋፅዖ ለማበርከት እንደሚያስችለው ጠቅሰዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ