ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጋዜጠኛ መስከረም አበራን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ስር የተከሰሱ 51 ግለሰቦች በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አንድ ጸረ-ሽብር ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
በዛሬው ዕለትም ዐቃቤ ሕግ የመጨረሻ ምስክር እንዲያቀርብ ቀጠሮ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬም ምስክሮቹ አለመቅረባቸው ተገልጿል።
ከዚህ ጋር ተያያዘም ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም፤ ምስክር እንዲያቀርብ በቂ ጊዜ የተሰጠው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ "ከአሁን በኋላ ምስክር አልቀበልም" ብሏል።
በዚህም የግራ ቀኙን ክርክር በመስማት መዝገቡን ለሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ብይን ለመስጠት የተቀጠረ መሆኑን አሐዱ በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል።

በእነ ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ሥር 51 ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ሕግ ከታህሳስ ወር አካባቢ ጀም ምስክር ሲያሰማ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ የመጨረሻ ምስክሮችን ለማቅረብ አካባቢዎቹ የጸጥታ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው ለማቅረብ እንደተቸገረ ለችሎቱ በጽሁፍ አስረድቷል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውና በቂ ምስክር እንደሚያቀርብ ችሎቱን ጠይቀዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ተከሳሾችና የተከሳሽ ጠበቆች ይህ ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው በመጥቀስ፤ "በተለይ የጸጥታ ችግርን ምክንያት በማድረግ ጉዳዩ እንዲጓተት ለማድረግ ነው" ብለዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ አካባቢዎች ሰላም እንደሆኑ እየገለጸ መሆኑን አንስተው፤ "በተለይም የተሽካርካሪ መንገዶችና አየር መንገዶች ክፍት ናቸው፡፡ ለምን ማቅረብ አይችልም" ሲሉ ለችሎቱ ጠይቀዋል።
አክለውም "ያለፍርድ ከ2 ዓመት 4 ወር ድረስ በእስር መቀመጥ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብትን የሚጋፋ በመሆኑ፤ ይህን ጉዳይ ችሎቱ ሊገነዘብልን እንወዳለን" ሲሉ ጠበቆቹ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር በማዳመጥ ከአሁን በኋላ ምስክር የማይቀበል መሆኑን በመግለፅ፤ መዝገቡን ለሐምሌ 4/2017 ብይን ለመስጠት ተቀጥሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ