ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ይህንን መልክት ያስተላለፉት በሪዮ ዲ ጄኒሮ እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው የብሪክስ ጉባኤ የሰላም፣ የፀጥታ እና አለምአቀፍ አመራር መድረክ መክፈቻ ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በዚህ የመክፈቻ ንግግር ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቢይ አሕመድ፤ "በአህጉሪቱ ስኬታማ ትብብርን ለማስቻል አፀፋዊ መተማመንን የሚያሳድጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማጠናከር የግድ ይላል" ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት ይረዳ ዘንድ የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅራቸው ምሉዕነት ባለው መልክ የሚሻሻልበትን ሁኔታ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በይፋ ወደ ብሪክስ የተቀላቀለችው በ2015 ዓ.ም ሲሆን፤ "ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ፍትኃዊ የሆነ፣ እኩልነት የሚሰፍንበት ብዝኃ ዋልታዊ አለምን ለመፍጠር ከሚተጉ ሀገራት ጋር በእኩል ደረጃ የተሰለፈችበት መድረክ ነው" ሲሉ አስታውቃዋል፡፡

"እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት ትሳተፋለችም ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡት፡፡

"ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለም አቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል" ሲሉም አድንቀዋል።

የደብብ አፍሪካዉ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው፤ ብሪክስ ጠንካራ የባለብዙ ወገንነት እና የተቀናጀ የሰላም ዲፕሎማሲን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የብሪክስ አባል ሀገራት ዓለም አቀፍ ግጭቶችን በማስታረቅ እና ዓለም አቀፍ አስተዳደርን በመቅረጽ ረገድ የበለጠ አስተማማኝ ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።

ራማፎሳ በንግግራቸው ቀጣይ ግጭቶችን ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

"በሩሲያ እና በዩክሬን፣ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሱዳን እና በጋዛ እና በሌሎችም ግጭቶች በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለው ከባድ ጉዳት በእጅጉ ያሳስበናል" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

አክለውም "ብሪክስ ለእነዚህ አስከፊ ግጭቶች ፍትሃዊ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ማግኘት አለበት” ብለዋል።

ራማፎሳ ብሪክስ በጂኦግራፊያዊ ተደራሽነቱ እና በጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታው እየጨመረ በመምጣቱ በዓለም አቀፍ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ጥሩ አቋም እንዳለው አድንቀዋል።

ህብረቱ ሁሉን የሚያጠቃልል፣ የሚወክል እና በሉዓላዊነት፣ በእኩልነት እና በሰላም አብሮ የመኖር መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀፍ እንዲፈጠር የጋራ ድምፁን እንዲያጠናክር ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

እንደ ሽብርተኝነት፣ የሳይበር ደህንነት እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ከሀገር አቀፍ ድንበሮች በላይ እየጨመረ በሚሄዱ እና የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ምላሾችን በሚሹ ጉዳዮች ላይ የብሪክስ የደህንነት ትብብርን እንደሚያስፈልግም መጠቆማቸውን አርቲ ኒውስ ዘግቧል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ BRICS አገሮች በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማስፋት ጥረት አድርገዋል።

እ.ኤ.አ. በ 2024 ቻይና እና ብራዚል በጋራ የዩክሬንን ግጭት ለመፍታት የሰላም እቅድ አቅርበዋል፡፡ ይህም ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በሌሎች የብሪክስ አባል ሀገራት ድጋፍ ተደርጓል።

በተጨማሪም ፕሪቶሪያ በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲቆም በመጠየቅ ድምጻዊ አቋም ወስዳ መቆየቷ የሚታወስ ሲሆን፤ በሰብዓዊ የመብት ጥሰት እስራኤል በሕግ ተጠያቂ እንድትሆንም ስትወተውት ቆይታለች።

ብሪክስ በአዉሮጵያኑ 2009 በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና የተቋቋመ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ከሁለት ዓመት በኋላ ተቀላቅላለች።
ባለፈው ዓመት ቡድኑ ሙሉ አባልነቱን ወደ ኢራን፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ኢንዶኔዢያ አስፋፍቷል።

በዛሬው ዕለትም የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ ጉባዔው ባወጣው የአቋም መግለጫ፤ "ኢትዮጵያ እና ኢራን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሀገራት እንዲሆኑ ሙሉ ድጋፍን" መስጠቱን አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ