ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 3ኛ ልዩ ስብሰባው፤ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ላይ፤ "መርማሪው ከግድያ ውጭ የትኛውንም ድርጊት ቢፈጽም ተጠያቂ አይሆንም" የሚለውን ድንጋጌ በማውጣት አዋጁን አርሞ አጽድቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በምክር ቤቱ የጸደቀው አዋጅ በሽፋን ሥር የሚደረግ ምርመራ (Undercover investigation) እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው፤ በግዴታ ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያትና ከፈቃዱ ውጪ በሆነ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም የሚል ነበር።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባው በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 49 (2)ሀ መሠረት ውሳኔ የተሰጠበት ድንጋጌ እንዲታረም በሚል፤ ከሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ መርምሯል፡፡

Post image

የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 37ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1387/2017 አድርጎ ማፅደቁ አስታውሰዋል፡፡

ከአሁን በፊት የነበረው የረቂቅ አዋጅ ድንጋጌ እንዲታረም መደረጉ አተገባበሩ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊያስከትል ስለሚችል ረቂቅ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 780/2005ን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ላይ ከነባሩ አዋጅ አንቀፅ 26 ንዑስ አንቀፅ (3) ቀጥሎ አዲስ ንዑስ አንቀፅ (4) ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑንም አቶ ኢሳ ቦሩ አብራርተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ለሰብአዊ መብት ጥሰት በር የሚከፍት በመሆኑ ድንጋጌውን መሻሻሉ ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፍትህ ተቋማት በምርመራ ሂደት ላይ በዜጎች አላስፈላጊ ድርጊት እንዳይፈፅሙ ክፍተት እንዳይሰጥ ለማስቻል የድንጋጌውን እርምት በጥሩ ጎን እንደሚረዱት የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 49 (2)ሀ መሠረት ድንጋጌው መሻሻያ ተደርጎበት፤ የውሳኔ ሃሳብ፤ ውሳኔ ቁጥር 11/2017 ሆኖ በአንድ ተአቅቦ፤ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ