መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እስራኤል እና ሃማስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን የጋዛ የሰላም እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ፤ ቀጥተኛ ያልሆነ አዲስ ዙር ድርድር ዛሬ በግብፅ ሻርም ኤል ሼክ ይጀመራል።

በዚህም የእስራኤል፣ የሃማስ እና የአሜሪካ ልዑካን ቡድን ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት ለማቆም፤ በትራምፕ የሰላም እቅድ ላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በእቅዱ ከተካተቱ ዋና ዋና ነጥቦች ውስጥ የሐማስ ትጥቅ መፍታት፣ በሕይወት ያሉ እና የሞቱ የእስራኤል ታጋቾችን በሙሉ መፍታት እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ መውጣት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በዚህም እስራኤል ይህንን ስምምነት በይፋ በተቀበለች በ72 ሰዓታት ውስጥ፤ ሁሉም በሕይወት ያሉ እና የሞቱ ታጋቾች ይመለሳሉ ይላል እቅዱ፡፡

Post image

ከስምምነቱ በኋላ በሚደረገው የመልሶ ግንባታ ወቅትም ፍልስጤማውያን ከፈለጉ በጋዛ ውስጥ ሊቆዩ እንደሚችሉ በእቅዳቸው የገለጹት ትራምፕ፤ ለሕዝቡ ጥቅም ሲባል ጋዛ እንደገና እንደሚገነባ አስታውቀዋል፡፡

ሃማስ ይህንን የትራምፕ ባለ 20 ነጥብ እቅድ በከፊል የተቀበለ ሲሆን፤ የእስራኤል ታጋቾችን መልቀቅን ላይም ሙሉ ለሙሉ መስማማቱን አስታውቋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ድርድሩ በግብፅ ሻርም ሼክ እንደሚካሄድ በማረጋገጥ፤ ተደራዳሪ ልዑካን ቡድኑ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ሚኒስትር ሮን ዴርመር እንደሚመራ በትናንትናው ዕለት አስታውቋል፡፡

Post image

በሃማስ በኩል ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ በዶሃ ኳታር በእስራኤል የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው፤ በካሊል አል-ሀያ የሚመራ ልዑክ በትናንትናው ዕለት ለድርድሩ ግብጽ ገብቷል፡፡

በዚህም ድርድር ላይ በአሜሪካ በኩል የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የቀድሞ የፕሬዚዳንት አማካሪ ያሬድ ኩሽነር እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱራህማን አልታኒ አደራዳሪ ሆነው እንደሚገኙ ተመላክቷል።

Post image

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትናትናው ዕለት ድርድሩን አስመልክተው በትሩዝ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ "አወንታዊ ውይይቶች በጣም በተሳካ ሁኔታ እና በፍጥነት እየሄዱ ነው" ብለዋል፡፡

"ሁሉም ሰው በፍጥነት እንዲንቀሳቀስ እጠይቃለሁ" ያሉት ትራምፕ፤ "የመጀመሪያው ምዕራፍ በዚህ ሳምንት መጠናቀቅ እንዳለበት ተነግሮኛል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ ወገኖች መካከል በአስቸኳይ ስምምነት እንዲደረግ ከፍተኛ ጫና በማሳደር ላ የሚገኙ ሲሆን፤ በዚህም "ጦርነቱን ወደ ፍጻሜው ያመጡ ሰው" ሆነው መታወስ ይፈልጋሉ፡፡

በዚህም በጋዛ ላይ የሚደረጉት እነዚህ ድርድሮች በፍጥነት ተከናውነው፤ አርብ በሚታወጀው የኖቤል የሰላም ሽልማት ላይ አበርክቷቸው እውቅና እንዲሰጠው ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ዛሬ የሚጀመረውን አዲስ ድርድር የሚያውቁ ከፍተኛ የፍልስጤም ባለስልጣን፤ በሃማስ እና በእስራኤል መካከል በግብፅ ከሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር በፊት በሃማስ፣ በኳታር እና በግብፅ ተወካዮች መካከል የቅድመ ዝግጅት ስብሰባዎች እንደሚደረጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ውይይቶቹ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም እቅድ ውሎች እና አፈፃፀሙ ላይ ያተኮሩ ናቸው ብለዋል።

Post image

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በጋዛ ከተማ ላይ እያደረሰችው ያለውን ጥቃት አሁንም አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፤ ባለፉት 24 ሰዓታት በጋዛ ላይ በሰነዘረችው ጥቃት 24 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል አታውቀዋል፡፡

"የቦምብ ድብደባው አሁንም አልቆመም" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ "ጥቃቱ ከአራት ሳምንታት በፊት ከተጀመረ ወዲህ ምንም አይነት የእርዳታ መኪና ወደ ጋዛ ከተማ እንዲገባ አልተፈቀደም" ሲሉም አክለዋል።

የትናንቱ የእስራኤል የአየር ድብደባዎች በከተማዋ በርካታ አካባቢዎች እንደመቱ የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፤ ጥቃቱ ትኩረት ያደረገው በደቡብ እና ምዕራባዊ ክፍሎች ኢንዱስትሪያል ዞን እና በዩኒቨርሲቲ አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ቴል አል-ሃዋ፣ አል-ጃላ እና አል-ናስር ጎዳናዎች በአንድ ሌሊት የቦምብ ጥቃቱ ካወደማቸው አካባቢዎች መካከል እንደሚገኙበት ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ