መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል አሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሁሉም ጥረት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤ በ2018 የትምህርት ዘመን እስከ መስከረም 20 ድረስ በተደረገው የምዝገባ ሂደት 'ይመዘገባሉ' ተብሎ ከተጠበቀው የተማሪዎች ቁጥር 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚሆኑት ብቻ መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ልጆችም ቢሮው 'ሊመዘገቡ ይችላሉ' ብሎ የጠበቃቸው እንጂ አጠቃላይ በክልሉ የሚገኙና እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱት በሙሉ የሚቆጠሩ ከሆነ ከትምህርት የራቁት ከዚህም በላይ ሊሆኑ እንደሚችል ተናግረዋል።

የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከ2 ሺሕ 400 በላይ ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ከ1 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከተባለለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ልጆችም የሥነ-ልቦና ጥቃትን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን እያሳለፉ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ይህም ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁናዊ ግጭት፣ ጦርነት በተካሄደባቸውና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ድርቅና የምግብ ውስንነት፣ ተፈናቃዮችና ሌሎች በክልሉ ያሉ ተደራራቢ ችግሮች መንስኤ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመንግሥት በኩል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ያነሱ ሲሆን፤ ሁሉም ባለድርሻ አካል ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በትምህርት ዘርፍ አዲስ የትምህርት ስርዓት ከመቅረፅ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን አንስተው በዚህም ጥሩ ውጤት ማምጣት መቻሉን የገለጹት ደግሞ፤ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ናቸው።

ከዚህ በተለየ መልኩ ግን በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አለመሄድ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ችግር በስፋት በሚስተዋልበት በአማራ ክልልም እስካሁን ድረስ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ በ2018 የትምህርት ዓመት ወደ ትምህርት ይመለሳሉ ተብሎ ከታቀደው ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ወደ ትምህርት መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ልጆት ወደ ትምህርት አለመመለሳቸው ከራሳቸው ከልጆች አልፎ በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም ለዓለም ትልቅ አበርክቶት የሚያደርጉ የነበሩት ሳይማሩ እንዳይቀሩ ሁሉም አካል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ