ጥቅምት 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የእስራኤል መንግሥት የጋዛ ሰርጥን ለመያዝ ወይም ለማስተዳደር ፍላጎት የለውም ሲሉ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል ኤምባሲ በጋዛ የሚንቀሳቀሰውና በምዕራባውያን ዘንድ በአሸባሪነት የተፈረጀው ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈፀመበትንና 1 ሺሕ 200 ሰዎች የተገደሉበትን እንዲሁም 251 ሰዎች ታግተው የተወሰዱበትን ሁለተኛ ዓመት ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በዛሬው ዕለት አስቦ ውሏል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ የእስራኤል መንግሥት ጋዛን ለመያዝ ወይም ለማስተዳደር ፍላጎት የለውም፡፡
"እስራኤል ጦርነት ውስጥ የገባቸው ሦስት አላማዎችን በመያዝ ነው" ያሉት አምባሳደር አብርሃም፤ ሀገሪቱ እነዚህን ግቦች ካሳካች መንግሥት ጋዛን ለማስተዳደር ወይም ለመቆጣጣር ፍላጎት የለውም ብለዋል፡፡
እስራኤል ከሃማስ ጥቃት በኋላ ወደ ጦርነት የገባችባቸውን ምክንያቶች ሲገልፁም፤ ታጋቾችን ማስለቀቅ፣ የሃማስን መንግሥታዊና ወታደራዊ ሃይል በመደምሰስ ጋዛ ወደፊት ለእስራኤል አስጊ እንዳትሆን ማድረግና አስተማማኝ የሆነ የደህንነት መዋቅር በደቡባዊ እስራኤል መመስረት ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህ ሂደትም እስራኤል በአሜሪካ አደራዳሪነት ከሃማስ ጋር የተኩስ አቁም በማድረግ የቀሩትን 48 ታጋቾች ለማስመለስ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሰኞ ዕለት 20 በሕይወት ያሉ ታጋቾችን ተረክባለች ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከቀሩት 28 የታጋች አስከሬኖች ውስጥ እስካሁን ሃማስ ለእስራኤል የመለሰው ዘጠኝ አስከሬኖችን ብቻ ነው ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም "ጦርነቱ ከሁለት ዓመት በላይ የፈደጀው ሃማስ አግቶ የወሰዳቸውን እስራኤላውያን እና የሌላ ሀገር ዜጎች አለቅም በማለቱ ነው" ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በአውሮፓውያኑ ኦክቶበር 7፣ 2023 በደቡባዊ የእስራኤል ክፍል ሃማስ የፈፀመው ድንገተኛ ጥቃት በእስራኤላውያን አቆጣጠር በዛሬው ዕለት ሁለተኛ ዓመቱን በመድፈኑ፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእስራኤል ኤምባሲዎች ዓለቱን እያሰቡ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ አሁንም ቢሆን ሃማስ መሳሪያውን ካስቀመጠና ታጋቾችን ሙሉ በሙሉ ካስለቀቀ እስራኤል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት በተካሄደው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከሁለት ዓመት በፊት በደቡባዊ የእስራኤል ክፍል ሐማስ በፈፀመው ድንገተኛ ጥቃት ታግተው ከተወሰዱት 251 ዜጎች ውስጥ አንዷ የነበሩትና ከ52 የእገታ ቀናት በኋላ ወደ ቤታቸው የተመለሱት ሶሻን ሃራን (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ዶክተር ሾሻን በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚገኙ አነስተኛ የእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ገበሬዎች በቂ ምርት እንዲያመርቱና ከምግብ እጥረት እንዲላቀቁ የማድረግ ተልእኮ እንዳለው የተገለጸው “Fair Planet” የተሰኘ ዓለማቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መስራችና ፕሬዝደንት ሲሆኑ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ሃማስ በሰነዘረው ጥቃት ባለቤታቸውንና ዘመዶቻቸውን ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም ከ52 ቀናት የሃማስ እገታ በኋላ መለቀቃቸውን ተከትሎ፤ ቀሪ ታጋቾች እንዲለቀቁና ድጋፍ እንዲደረግላቸው የማስተባበር ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
"ሽብርተኞችን የሚደግፍ አካል ባይኖር ሃማስ ይህንን መሰሉን ጥቃት ለመፈፀም አቅም አይኖረውም ነበር" ያሉት ሾሻን፤ ቀሪው ዓለም ሽብርተኝነትን መደገፍ መቆም አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ