ሰኔ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሂጅራ ባንክ በ2024/25 የበጀት ዓመት ከ840 ሚሊየን ብር በላይ በማትረፍ፤ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ገቢ ማስመዝገቡን አስታውቋል፡፡
ይህም ባለፈው ዓመት ካስመዘገበው ጠቅላላ ገቢ የ148 ነጥብ 85 በመቶ እድገት ማሳየቱን የገለጸው ባንኩ፤ የሦስተኛ ዓመት የእድገት ስትራቴጂ በመተግበር ላይ መሆኑ ለዚህ ዓመት ስኬታማነቱ አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጿል፡፡
በዚህም ባንኩ በዚህ ዓመት ያገኘው የ840 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ፤ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 740 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑን አስታውቋል።
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ከ15 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጸም ሲሆን፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 95 ነጥብ 37 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው ብሏል።
እንዲሁም የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 12 ቢሊዮን ብር በማሳደግ፤ 91 ነጥብ 4 በመቶ ስኬታማ የእድገት ውጤት ማስመዝገቡንም ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በተጨማሪም 40 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን በመግለጽ፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 304 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡን ገልጿል።
ባንኩ የማክሮ ኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታዎችን ተጽዕኖ በመቋቋም ተደራሽነቱን በማስፋት 135 ቅርንጫፎች መክፈቱን ያስታወቀም ሲሆን፤ "በ2024/25 የበጀት ዓመት 35 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለአገልግሎት ክፍት አድርጌያለሁ" ብሏል።
እንዲሁም አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ጠቅላላ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 931 ሺሕ 148 ማድረሱን አስታውቋል፡፡
ከዲጂታል አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ የኦምኒ ፕላስ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ350 ሺሕ በላይ መሆኑን የገለጸም ሲሆን፤ ባለፉት 6 ወራት ብቻ የሀላል ፔይ ዋሌት ተጠቃሚዎች ከ811 ሺሕ በላይ መድረሳቸውንም በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ባንኩ ከመሰረታዊ የባንክ አገልግሎቶች በተጨማሪ ያለ ማስያዣ የፋይናንስ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችል ኢ-ሙራበሃ የፋይናንስ አገልግሎትን በዋሌት በማስጀመር ስኬታማ ዓመትን ማሳለፉንም ነው ያስታወቀው።
እንዲሁም ከ20 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በዲጂታል በኩል መንቀሳቀሱን የገለጸው ባንኩ፤ "አጠቃላይ ከተደረገው የገንዘብ ዝውውር ውስጥ 34 ነጥብ 52 በመቶው በዲጂታል መንገድ የተከናወነ ነው" ብሏል፡፡
ሂጅራ ባንክ በ2024/25 የበጀት ዓመት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማስቀደምና ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጿል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ