ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳደግ በባቡር በዓመት የምታጓጉዘውን 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ካርጎ ወደ 4 ሚሊዮን ለማሳደግ እየተሰራበት እንደሚገኝ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ በዋናነት በጅቡቲ ታጁራ ወደብ የሚከናወን እንደሆነ የገለጹት የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ፤ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውም በዚሁ ወደብ እንደሚያልፍ አንስተዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው አክለውም፤ ኢትዮጵያ የምታጓጉዘው የካርጎ መጠንም በዓመት 18 ሚሊዮን ቶን አካባቢ መድረሱን አስታውቀዋል።
ከእዚህም ውስጥ ባለፉት ዓመታት በተሰራ ሥራ ካርጎዎችን በባቡር ማጓጓዝ መጀመሩን ያስታወሱ ሲሆን፤ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ካርጎ በተሽከርካሪ እንደሚጓጓዝ ገልጸዋል።
አሁን ያለው የባቡር አቅርቦት ከ6 እስከ 10 ሚሊዮን ቶን ካርጎን በዓመት ማጓጓዝ እንደሚችል ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው፤ በአሁኑ ወቅት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ብቻ በባቡር እየተጓጓዘ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም በዚህ ዓመት 4 ሚሊዮን ቶን እንዲደርስ ለማድረግ እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በተሽከርካሪ ሲጓጓዝ የመንገዶች ችግርና ርዝመት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጅቡቲ ውስጥ ባለው የመንገድ ብልሽት ምክንያት ተሽከርካሪዎች እስከ አራት ቀን ድረስ ሊቆዩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
"ሎጀስቲክስ ላይ ዋናው ነገር ጊዜ ነው" ሲሉ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተሽከርካሪ ማጓጓዝ ጊዜ ከመውሰዱ ባሻገር ዋጋን በመጨመር የንግድ ተወዳዳሪነትን ይገድባል ብለዋል።
ለአብነትም በአማካኝ በወር 28 ሺሕ በላይና በቀን ደግሞ ከ1 ሺሕ 500 በላይ ተሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደብ ገብተው እንደሚወጡ በማንሳት፤ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ነዳጅን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
በመሆኑም እነዚህ ችግሮችን ለመቅረፍ የካርጎ አገልግሎትን በባቡር እንዲሆን ማድረግ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የማዳበሪያ እና የዘይትን የመሳሰሉ ለሕብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑና በልዩነት የሚታዩ ካርጎዎች በባቡር ሲጓጓዙ በፍጥነት እና በተሻለ ዋጋ ይደርሳሉ ብለዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም 95 በመቶ የሚሆነው ቡና ወደ ውጪ የሚላከው በባቡር ትራንስፖርት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም በቡና ብቻ በዓመት በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር እየተገኘ እንደሆነ ተናግረዋል።
በገቢና ወጪ ንግድ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ተቋማትም ለካርጎ አገልግሎት የባቡር ትራንስፖርትን መጠቀም እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ