ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ለቁም እንስሳት ልማት እና ለአርብቶ አደሮች ድጋፍ ከዓለም ባንክ በተገኘ የ20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር የተጀመረው ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም፤ ተጠቃሚ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ እንደሚለው፤ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልቶ የብድር ድጋፉን መውሰድ የቻለው አንድ ማኅበር ብቻ ነው።
የብድር ድጋፉ ተጠቃሚ የሚሆኑት በ5 ክልሎች ማለትም፤ በአፋር፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮች ናቸው ተብሏል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዕውቀት አስተዳደር ሥልጠና ባለሙያ አቶ ተሾመ ኃይለ ገብርኤል ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ለብድር ድጋፉ 396 የሚሆኑ ድርጅቶች በግብርና ሚኒስቴር በኩል ቢቀርቡም፣ ብድሩን የወሰደው ግን አንድ ማኅበር ብቻ ነው።
ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት የቀረቡት ማኅበራት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያወጣቸውን የቋሚ ንብረት ማስያዣ መስፈርቶች ማሟላት ባለመቻላቸው ነው ተብሏል።
የብድር ድጋፉ የተያዘበት ዋነኛ ምክንያት ለኤክስፖርት ከሚቀርቡ የቁም እንስሳት መካከል 91 በመቶ የሚሆነው ከአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚመጣ በመሆኑ፤ በዘርፉ ያለውን ምርታማነት ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

ፕሮጀክቱ የቁም እንስሳት ንግዱን አሳልጦ የአርብቶ አደሩን እንስሳት ወደ ገበያ የሚያቀርብበትን ሁኔታ ያመቻቻል ያሉም ሲሆን፤ በዚህም የኢንሹራን አገልግሎት መስጠት፣ የአርሶ አደሩን የቁጠባ ባህል መበረታታት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ወይንም የሞባይል መተግበሪያዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ላይ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ሥር በዘርፉ ያሉትን መሠረተ ልማቶች ማሻሻል፣ አርብቶ አደሮች እና እንስሳትን ወደ ውጪ የሚልኩ ነጋዴዎች በአንድ የሚገናኙበትን ማዕከሎች መገንባት እንዲሁም፤ በግል ደረጃ የተሰማሩ የስጋ አቅራቢዎችን እና የቁም እንስሳትን ወደ ውጪ የሚሸጡ ነጋዴዎች እና ማህበራትን መርዳት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም 20 ሚሊየን ብር ብድር በሁለት መንገዶች ለመስጠት መታሰቡን የገለጹት አቶ ተሾመ፤ የመጀመሪያው በእንስሳት ሀብት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የግል ነጋዴዎችን ወይንም ኢንቨስተሮችን መርዳት ሲሆን በዚህም ለግል ባለሀብቶቹ እስከ 600 ሺሕ ዶላር የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት ብድሩ ለ6 ሰዎች ይሰጣል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፤ ብድሩን ለማግኘት 40 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በራሳቸው ማዘጋጀት የሚጠብባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 60 በመቶውን ደግሞ በልማት ባንክ በኩል ፕሮጀክቱ የሚደግፋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛው የፕሮጀክቱ ትግበራ በአርብቶ አደር ደረጃ የተደራጁ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ማህበራት የሚሠጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"አብዛኞቹ እስካሁን ድረስ ያሉ ፕሮጀክቶች ልማት ላይ ነው የሚሰሩት" ያሉት ባለሙያው፤ ይህ ፕሮጀክት ከዚህ በፊት የነበሩትንም ሆነ በተጓዳን ሌሎች የሚሰሩትን ወደ ገበያ መውሰድ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2023 ጥር ወር ላይ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወሱም ሲሆን፤ ገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ቀጥታ ለልማት ባንክ ገንዘቡን መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ደብረዘይት አካባቢ የሚገኝና እንስሳቶችን ከአርብቶ አደር አካባቢ ሰብስቦ ወደ ውጪ የሚልክ አንድ ባለሃብት ብቻ ከሁለት ሳምንት በፊት የሚጠበቅበትን መስፈርት በማሟላት ብድሩን ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የብድር ድጋፍ የወሰደው አንድ ባለሃብት ቢሆንም፤ በዘርፉ ላይ እየሰራ ስለመሆኑ ግን ግልጽ መረጃ አለመኖሩን አስታውቋል።
አሐዱ ስለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ምላሽ ሲያገኝ ዘገባውን ይመለስበታ፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ