መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትጵያ አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወደ አለ ደረጃ የተሸጋገረ ሲሆን፤ ይህ ፍትሃዊ ጥያቄያችንም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘት ችሏል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና የፌዴሬሽን ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

በዚህም የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ምክር ቤቶቹ ዓመታዊ ሥራቸውን መጀመራቸውን ያበሰሩት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ በርካታ ሀገራዊ ፖለቲካዊ፣ ማህራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይዎች ላይ የተሰሩ ሥራዎች እና የቀጣይ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በንግግራቸውም መንግሥት የውጭ ግንኙነት ላይ ትኩረት አደርጎ መስራቱን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ "የውጪ ግንኙነታችን ማዕከልና መሰረታዊ ማጠንጠኛው ብሄራዊ ጥቅምና የዜጎች ክብር ነው" ብለዋል፡፡
በዚህ መነሻነትም "የኢትዮጵያ የጂኦ ስትራቴጂያዊ ቁመና በመደርጀት ላይ ይገኛል" ያሉ ሲሆን፤ ይህ ስትራቴጂያዊ ምርጫ ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማሸጋገር ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
"ሀገራችን በድንበር ተሻገር ሀብቶቿ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ስትቀበል፤ በዛው ልኬታም አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብቷን ማረጋገጥ ይኖርባታል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህልውና መሠረት በሆኑት በሁለቱ ታላላቅ የውሃ ሀብቶች ዙሪያ መንግሥት ያልተቆራረጠ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ እስከ አሁን በተደረጉ ጥረቶች ሦስት ጉልህ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የነበሩትን ፈተናዎች በጥበብ በማለፍ ማጠናቀቅ እና በደመቀ ሥነ-ስርዕት ማስመረቅ መቻሉ ነው ብለዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወደ አለ ደረጃ የተሸጋገረ መሆኑ ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህ ፍትሃዊ ጥያቄያችንም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ሌላው እና ሦስተኛው ደግሞ በውጭ ሀገር ለእንግልት እና ለችግር የተጋለጡ ዜጎች በክብር ወደ ሀገር የተመለሱ ሲሆን፤ ወደ ፊትም ይኸው ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የልማት ግንባታ ይሳተፉ ዘንድ ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በዲፕሎማሲ እና ቀጠናዊ ጉዳይዎች ላይ የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ችግር እንዳይፈጠር መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
የአባይ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የገለጹም ሲሆን፤ በቀጣይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራበት አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በርካታ ጉዳይዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ከስርዓት መለዋወጥ ጋር የማይቀያየር ብሔሄራዊ ደህነነትን ጨምሮ ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማትን የመገንባት ሥራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
ግጭቶችን መንግሥት በሀይል ለመፍታት አቅም ያለው ቢሆንም፤ ቂም እና ቁርሾን ላለማውረስ በውይይት እና በእርቅ እንዲፈታ እያደረገ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ በምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የመልካም አስዳደር ችግር እንዲፈታ፣ ፍትህ እንዲረጋገጥ እንዲሁም የትምህርት ጥራት እንዲሻሻልና ሌሎች ጉዳዮች ላይም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ