መስከረም 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባህልና ትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገበውና በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የአኝዋ ደን፤ ከአሁን ቀደም ከተመዘገቡ 5 የሥነ-ምህዳር ደን ቦታዎች አጠቃላይ ስፋት ጋር የሚስተካከል መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ስድስተኛው የሥነ-ምህዳር ደን የሆነውን 'አኝዋ' ቻይና በተካሄደው 37ኛው የዩኔስኮ አይሲሲ ኮንፈረንስ ላይ ማስመዝገቧ ይታወሳል።
የአኝዋ ደን ከአሁን ቀደም ከተመዘገቡት አጠቃላይ ስፋት የሚስተካከል በመሆኑ ለየት እንደሚያደርገው በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ግርማ እሸቱ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በዩኔስኮ ሦስት መርሃግብሮች እንዳሉ ያነሱት ተመራማሪው፤ የአኝዋ ደን የተመዘገበው 'ሰውና ተፈጥሮ' በሚባለው ዘርፍ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የአኝዋ ደን ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ስፋት እንዳለው ያነሱም ሲሆን፤ በዩኔስኮ ለመመዝገብ የቻለው በሦስት ጉዳዮች መሆኑንም አብራርተዋል።
እነዚህም አንደኛው የብዝሃ ሕይወት ሃብቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው የአካባቢው ማህበረሰብ እውቀት ማለትም ከአካባቢው ተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የመኖር ባህል እንደሆነ ገልጸዋል።
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ በዘላቂነት ልማትና ምርምር ላይ ባለው አስተዋጽኦ መሆኑን ጠቁመዋል።
ደኑ መዝገቡ በብዝሃ ሕይወት ጥበቃ በኩል እንደ ሀገር ለተያዘው ስትራቴጂ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ተመራማሪ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የሰውን የልማት ፍላጎት እና የተፈጥሮ ጥበቃን አዋህዶ የሚሄድበት በመሆኑ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም በዓለም አቀፍ ደረጃ የምርምር ቦታ በመሆን 'የሰው ልጅ እንዴት ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር ይችላል' ለሚል የምርመር ፅንሰ ሀሳብ አስተዋጽኦ በማድረግ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
በሌላ በኩልም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ቦታ በመሆኑ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው እንዲሄዱ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ፤ በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል።
"ቦታውን ማስመዝገብ ብቻ በቂ አይደለም" ያሉት ተመራማሪው፤ በቀጣይ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ