ሕዳር 2/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 'ሲቢኢ በእጄ' የተሰኘ አዲስ የዲጂታል ቁጠባ እና ብድር አገልግሎት በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል።
ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ በዲጂታል ባንክ አገልግሎት ብቻ ከ13 ትሪሊየን ብር በላይ ዝውውር መደረጉን፤ የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።

አሰራሩን በማዘመንም በዛሬው ዕለት 'ሲቢኢ በእጄ' የተሰኘ አገልግሎትን ማስጀመሩን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፤ አዲሱ አገልግሎት በደመወዝ መጠን ከ500 እስከ 150 ሺሕ ብር ድረስ ብድር ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአገልግሎቱ የመንግሥት ሠራተኞችን ቅድሚያ በመስጠት ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በማዕከል ደረጃ እና በዲስትሪክቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ አንስተዋል።
አገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በመስሪያ ቤቶቹ መካከል አጭር እና ግልፅ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በሲቢኢ ብር እንዲከፈል እንደሚደረግ የገለጹም ሲሆን፤ አገልግሎት አሰጣጡ በቀጣይ ሁሉንም ያማከለ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

ባንኩ እስከአሁን ባለው ጊዜ ከ478 ኩባንያዎች ጋር መደበኛ ስምምነቶች ተፈራርሞ ስምምነቶች ከፀደቀላቸው 83 ድርጅቶች የተወጣጡ ሠራተኞች በ'ሲቢኢ በእጄ' ዲጂታል ባንክ ብድር የተሰጣቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በብድር መስጠቱን ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ