ሕዳር 2/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ችግሮች እና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት ሕዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።

መድረኩን የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር እና ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንደስትሪ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ተነስቷል።

በመድረኩ የሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች ተሞክሯቸውን ለማካፈል ተገኝተዋል። ይህ መድረክ ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችልም የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ያሬድ ሞላ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት 19 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዳሉ ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ 'እነዚህ ኩባንያዎች እንዴት ማደግ እና መበልፀግ ይችላሉ?' የሚለውን አጀንዳ ከመንግሥት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ይህም በዋናነት እንደ ችግር የሚነሳ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ገለልተኛ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አለመቋቋሙ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ የኢንሹራንስ ኢንደስትሪው ራሱን ችሎ የሚተዳደር ከሆነ ፈጣን እድገት እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፤ ይህም በጥናት የተረጋገጠ እና በሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ መታየቱንም ገልጸዋል።

በብሔራዊ ባንክ በኩል ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ተቋቁሞ ወደተግባር እንደሚገባ ያስታወቀ ቢሆንም፤ እስካሁን ተግባራዊ እንዳልተደረገ አንስተዋል። ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ገለልተኛ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የሌላት ብቸኛ ሀገር እንደሆነች ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ