ጥቅምት 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከዋና የባቡር መስመር ግንባታ ሥራዎቹ ጎን ለጎን የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከር የተለያዩ አማራጭ ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ኮርፖሬሽኑ ራሱን ለማዳበር እየሠራ መሆኑ የተገለጸው፣ የባቡር ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ብሔራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

Post image

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሕሊና በላቸው (ኢ/ር)፤ ኮርፖሬሽኑ ሕዳር 2002 ዓ.ም. በዘመናዊ የባቡር አገልግሎት አማካኝነት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ታስቦ እንደተቋቋመ ገልጸዋል።

የኮርፖሬሽኑ ራዕይ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የባቡር መስመር በመገንባት ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የተሳሰረች በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ማጠናከር እንደሆነም አስረድተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኮርፖሬሽኑ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ያከናወናቸውን ሥራዎች በማንሳት፤ የአዲስ አበባን ቀላል ባቡር እንዲሁም ከአዲስ አበባ - ሰበታ - ደወሌ፣ የሞጆን እና የድሬዳዋን የባቡር መስመሮች ጠቅሰዋል።

Post image

በተጨማሪም ከአዋሽ ኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ፣ ከወልዲያ/ሐራገበያ-መቀሌ ያለው የባቡር መስመር እና የሶፍ ዑመር የባቡር ኢኮ ቱሪዝም መስመር በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢንጂነሪንግ ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦሜ በበኩላቸው፤ የባቡር አገልግሎትን ማዘመን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ በባቡር መሰረተ ልማት ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች መሆኑን አረጋግጠዋል።

Post image

በተለይም የኢትዮ-ጅቡቲን እና የኢትዮ-ኬንያን የባቡር ዝርጋታ በማንሳት፣ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ዕድገት አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ