ጥቅምት 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፍሪካ ያለው የውኃ ሀብት አጠቃቀም ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ፣ ከከተማ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ውጪ ባሉ እንደ መስኖ ያሉ ዘርፎች ላይ አነስተኛ ሥራ መሠራቱ ተገልጿል።

ይህ የተባለው "የዲጂታል መፍትሔ ለአፍሪካ የውኃ አስተዳደር" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በተጀመረው ዓለም አቀፍ የውኃ ሀብት አስተዳደር ጉባኤ ላይ ነው።

ጉባኤው አፍሪካ ያላትን የውኃ ሀብት በመረጃ ላይ ተደግፋ የምትጠቀምበትን ዕድል ለማስፋት ያለመ ነው ተብሏል።

ዓለም አቀፉ የውኃ አስተዳደር ተቋም የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ዓብዱልከሪም ሑሴን (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ ያለው የውኃ ሀብት አጠቃቀም በሚገባው ልክ አይደለም፤ የተሠራውም ሥራ አብዛኛው የከተሞችን የመጠጥ ውኃ ማዳረስ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው።

Post image

ዶክተር ዓብዱልከሪም በተጨማሪም፤ "በሌሎቹ ዘርፎች ማለትም በመስኖ በሌሎቹም ዘርፎች ላይ የተሰራው ሥራ አነስተኛ ነው። ይህ ደግሞ የመረጃ ክፍተት ያመጣው በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት እና ዲጂታል የመረጃ ሥርዓቶችን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ነው።" ብለዋል፡፡

በዚህ ክፍተት ምክንያት አህጉር አቀፍ በሆነ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ የጎርፍ፣ የድርቅ እና የውኃ እጥረት ችግሮች እየጨመሩ ነው ተብሏል።

በቂ ያልሆነ የመረጃ ሥርዓት መንግሥታት ቀድመው ችግሮችን አውቀው በፍጥነት ምላሽ እንዳይሰጡ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

ችግሩን ለመፍታት ዓለም አቀፉ የውኃ አስተዳደር ተቋም በኢትዮጵያ ከስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓይሻል ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ለማስፋፋት እየሠራ መሆኑ ተነግሯል።

የ2024 የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ አህጉሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል ውኃን ጨምሮ በእቅዳቸው መሠረት እየተጓዙ ያሉት 600 የሚሆኑት ሀገሮች ብቻ ናቸው።

በመሆኑም ክፍተቱን ለመሙላት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በውኃ ዘርፉ ላይ ማስፋት ችግሩ እንዲቀንስ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ