ጥቅምት 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያቋቋመው የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡
የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ የሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች፣ ሠልጣኞች፣ አጋር አካላት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ማዕከሉ የመገናኛ ብዙኃንና የማስታወቂያ ዘርፉ ወቅቱ በሚጠይቀው ሙያና ቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲሰራ የባለሙያዎችና የሚዲያ ተቋማትን አቅም የመገንባት ዓላማ የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ እና የመገናኛ ብዙኃንን አቅም ከማሳደግ አንፃር የላቀ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የልህቀት ማዕከሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር፣ ሕጎችና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እንደሚሰጥ ባለስልጣኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልኅቀት ማዕከል ከዚህ በፊት ከሚከናወኑ የመገናኛ ብዙኃን ክትትል እና ቁጥጥር ተግባራት ባለፈ ወደ አቅም ግንባታ የሚያሳድግ እንደሆነ በመድረኩ የተገለጸም ሲሆን፤ ማዕከሉ ጋዜጠኞች በትምህርት ቤት ከሚወስዱት ትምህርት ባሻገር የጋዜጠኝነት ሙያዎች ላይ ብቁ የሚሆኑበት ሥልጠና እንደሚሰጥም ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ