ጥቅምት 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት የተማሪዎች ውጤት እየተሻሻለ መምጣቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ሚኒስትሩ በጋምቤላ ክልል "የትምህርት ፍትሃዊነትና ጥራት ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው ክልል አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል።

Post image

በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ዘርፉ በተተገበሩ የሪፎርም ተግባራት በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸው አብራርተዋል።

አክለውም እንደ ሀገር ዘላቂ ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ በራሱ የሚተማመን ዜጋ መገንባት ያስፈልጋል፤ ለዚህም በትምህርት ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በጋምቤላ ክልልም በተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ መኖሩን ጠቅሰው፤ ለውጡን ይበልጥ ለማጠናከር አመራሩ በላቀ ቁርጠኝነት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በትምህርት ሽፋን የተሻለ ስኬት መመዝገቡን ገልጸው፤ ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

Post image

በክልሉ የትምህርት ተሳትፎንና ጥራትን ለማረጋገጥ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ