ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሦስተኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ25 በላይ የአፍሪካ ሚኒስትሮች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በአድዋ ሙዚየም ተጀምሯል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋየን ጨምሮ ከ25 በላይ የአፍሪካ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ "ፎረሙ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሥራ ገበያ አሠራር እና ፖሊሲዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች ውጤታማነት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ አለው" ሲሉ ተናግረዋል።

"መንግሥታት በሚቀጥሉት 2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳን በመቅረፅ፤ በአህጉሪቱ የሚታየውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የብይነ መረብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ሲሉ ነው የገለጹት።
መንግሥታት የሥራ እድል አቅርቦትን እና የሥራ ገበያ ፖሊሲዎችን በማዘመን ጥሩ የሥራ ዕድል ፈጠራን እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ሊያመጡ የሚችሉ የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ስለሆነም ጥሩ የሥራ ገበያ አስተዳደር ፍላጎትና፣ የሥራ ገበያ መረጃን መሰብሰብ፣ ማከማቸት፣ መተንተን፣ ማሰራጨት እና መከታተል የሚችሉ ተቋማት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ማውጣት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።
"የሠራተኛ ገበያ መረጃ ስርዓት (LMIS) ተገቢ እና ተፈፃሚነት ያለው የፖሊሲ፣ የፕሮግራም አወጣጥ እና አተገባበር አቅምን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ነው" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ "ከሥራ ገበያ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማዘጋጀት፣ ማከማቸት፣ ማሰራጨት እና አጠቃቀምን በተመለከተ የጋራ እውቅና ያላቸው ሚናዎችንና ስምምነቶችን ማሳካት ያስፈልጋል ሲሉ" አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ