ሰኔ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከብሪክስ ጉባዔ ጎን ሆነው፤ የአሜሪካንን ጥቅም የሚፃረሩ ሀገራት ተጨማሪ የ10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው አስጠንቅቀዋል።
17ኛው የብሪክስ ጉባዔ የሰላም፣ የጸጥታ እና ዓለም አቀፍ አመራር መድረክ በብራዚል በሪዮ ዲ ጄኒሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የአባል ሀገራቱ መሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህም የሁለት ቀናት ስብሰባ እያደረጉ ያሉት የብሪክስ መሪዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ የንግድ ግጭቶችና ጂኦፖለቲካል ውጥረቶች እየተባባሱ በመጡበት ወቅት ጥምረቱን የዲፕሎማሲ መድረክ አድርገው አስቀምጠዋል።
የብሪክስ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ዕሁድ እለት በሰጡት መግለጫም፤ ታሪፍ ለዓለም ኢኮኖሚ ስጋት መሆኑን በመግለጽ "በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እርግጠኛ አለመሆንን አስከትሏል" ሲሉ ነቅፈዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በብሪክስ ሀገራት መካከል ንግድን በማበረታታት እና አማራጭ የክፍያ ሥርዓቶችን በመዘርጋት ከምዕራባውያን ምንዛሬዎች ጥገኛነት መውጣትን ዓላማው ያደረገውንና ቻይና፣ ሩሲያ እና ህንድን አባል ያደረገውን ይህንን ጉባዔ በበርቱ ሲነቅፉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "ከብሪክስ ፀረ-አሜሪካ ፖሊሲዎች ጋር የሚሰለፍ ማንኛውም ሀገር ተጨማሪ 10 በመቶ ቀረጥ ይከፍላል። ለዚህ ፖሊሲ ምንም ልዩ ሁኔታዎች አይኖሩም" ሲሉ ገልጸዋል።
ሀገራት ከአሜሪካ ጋር የታሪፍ ውል የሚስማሙበት ቀነ ገደብ ለሐምሌ 2 ቀን 2017 ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት አሁን በነሀሴ ወር መጀመሪያ ላይ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
በዚህም እስካሁን ድረስ አሜሪካ ከእንግሊዝ እና ቬትናም ጋር የንግድ ስምምነቶችን ያደረገች ቢሆንም፤ እንግሊዝ እና አሜሪካ አሁንም በአሜሪካ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የእንግሊዝ ብረት ምርቶች ታክስ ላይ ስምምነት ላይ አልደረሱም።
ትራምፕ በፈረንጆቹ ጥር ወር ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካን ምርት እንደሚያሳድጉ በመግለጽ፤ ከሌሎች ሀገራት በሚመጡ ምርቶች ላይ ተከታታይ ቀረጥ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2024 ትራምፕ የብሪክስ ሀገራት የአሜሪካ ዶላርን ለመወዳደር ከሞከሩ፤ በሀገራቱ ላይ 100 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ መዛታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት የብሪክስ አባላት ሥም ዝርዝር ውስጥ ከመስራቾቹ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ፤ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ተካተዋል።
በተጨማሪም ጉባኤው 10 ሀገራት ማለትም ቤላሩስ፣ ቦሊቪያ፣ ኩባ፣ ካዛክስታን፣ ማሌዥያ፣ ናይጄሪያ፣ ታይላንድ፣ ኡጋንዳ፣ ኡዝቤኪስታን እና ቬትናምን የጥምረቱ አጋር አድርጎ ተቀብሏል።
በሕብረቱ ውስጥ ያሉት ሀገራት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ይሸፍናሉ።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ