መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ከበባ ለመፍጠር ወደ ምስራቅ አፍሪካ እግሯን ለመትከል እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ ማክሸፍ የሚቻለው፤ ስትራቴጂካዊ የድፕሎማሲ አካሄድን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ሲቻል ነው ሲሉ የቀድሞ ዲፖሎማቶች ለአሐዱ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲዋን ጤናማ አድርጋ ማስቀጠል ከቻለች፤ በጠላትነት የሚከሷት ሀገራት እንዳይተባበሩባት ይረዳታል ሲሉ የቀድሞው ዲፕሎማት ዴያሞ ዳሌ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ለአብነት ኢትዮጵያ የራሷ ንብረት በሆነው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ግብፅ የ'ይገባኛል' ጥያቄ ለዓመታት ስታነሳ ቆይታ ሲከሽፍባት፤ አሁን ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ እግሯን በመትከል በኢትዮጵያ ከበባ ለመፍጠር እየተቀሳቀሰች መሆኑ ይታወቃል።

አቶ ዴያሞ "ይህ ማክሸፍ የሚቻለው፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እየተስተዋሉ ያሉ የዲፖሎማሲ ብልሽቶችን የኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ መልስ ከመመለስ ተቋጥቦ፤ ችግሩን ለመፍታት ጥበብ የተሞላበትና በጥልቀት የተጠናበት የዲፖሎማሲ መርህ ሲከተል ነው" ብለዋል።

እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ድንበር ማስቀመጥ የግድ ቢሆንም፤ ሕዝብ ለሕዝብን ግንኙነትን ሊያለያይ የሚችል ድንበር መዝጋት አያስፈልግም ሲሉ ዲፕሎማቱ ለአሐዱ ገልጸዋል።

ከላይ ያለውን ሃሳብ የሚጋሩት ሌላኛው የቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በበኩላቸው፤ የግብፅ ተባባሪ ከሆኑ ሀገራት፤ ማለትም ከኤርትራ፣ ሶማሊያና ጁቡቲ ጋር ያለው የዲፕሎማሲ ነባራዊ ሁኔታ ሲገመገም ሊጨበጥ የሚችል አይደለም ብለዋል።

ሆኖም "በመንግሥታት መካከል የዲፕሎማሲ ብልሽት ሲያጋጥም በፍጥነት ለማበላሸት ተባባሪ መሆን አይጠበቅም" ሲሉ ገልጸው፤ በመንግሥትንና በሕዝብ መካከል ልዩነት ስላለ፤ በአንዴ ሁሉንም ግንኙነት ማቋረጥም የችግሩን መጠን ሊያገዝፈዉ ስለሚችል ጥንቃቄ የተሞላበት ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር የወታደራዊ አቅሟን ማሳደግና የውስጥ ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት በማድረግ፤ ከጎረቤት ሀገራት አልፎ አልፎ እያጋጠመ ያለውን ዲፖሎማሲያ ችግር ለመፍታት መንግሥት አሁንም ለሰላማዊ ድርድር ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅባታል ሲሉ ዲፕሎማቶቹ ለአሐዱ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ