ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ታሳቢ ያደረገ እና ኢትዮጵያን ከሁሉም የጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስር የባቡር መስመር እየተሰራ እንደሚገኝ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።
የባቡር ትራንስፖርት ኢንቨስትመንት ከፍተኛ በመሆኑ ረዥም ርቀትን፣ መሰረተ ልማትን እንዲሁም ንግድና ቀጠናዊ ትስስርን ታሳቢ አድርጎ እንደሚሰራ የገለፁት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ናቸው።
በመሆኑም የባቡር መስመር ዝርጋታ በሀገር ውስጥ የሚቆም ሳይሆን፤ በሁሉም አቅጣጫ ከሚገኙ ጎረቤት ሀገራትና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ ለመነገድና ለመስራት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ባሻገር ደግሞ የአፍሪካን አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ከማስፋፋት አንፃር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ሲባል ወደሁሉም የጎረቤት ሀገሮች መንገዶች እየተሰሩ መሆኑን የሚገልጹት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም መሆኗን አክለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ለአብነትም ከኬንያ ወደቦች እስከ ሞያሌ ድረስ ያለው መስመር በተሳካ ሁኔታ መሰራቱን አንስተዋል።
"ኢትዮጵያ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል እንደሆነች ሁሉ የቀጠናዊ ትስስሩንም ግንባር ቀደም እየሆነች ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪአሁን ላይ በባቡር ትራንስፖርት ከጅቡቲ ጋር ትስስር መኖሩን የገለጹ ሲሆን፤ መስመሩ ብቻም ሳይሆን ድርጅቱም በሁለቱ ሀገራት በጋራ እንደሚተዳደር አንስተዋል።
ይህም አንድን ተቋም እና መሰረተልማት በጋራ ገንብቶ አብሮ በመጠቀም በኩል ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
ይህ የባቡር መሰረተልማት እየተስፋፋ ሲሄድ ወደ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ኬንያ እና ወደ ሌሎችም ጎረቤት ሀገራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠናን ታሳቢ ያደረገ የባቡር መስመር ትስስር ወደ ሁሉም የጎረቤት ሀገራት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ