ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በሞዴሊንግ የስልጠና ዘርፍ በ1996 ዓ.ም ተመስርቶ በፋሽን ዲዛይኒንግ የስልጠና ዘርፍ በ1999 ዓ.ም ሙሉ እውቅና በማግኘት ሥራውን የጀመረው ኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ፤ 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ አርቲስት ሀመልማል አባተ እና አርቲስት መቅደስ ጸጋዬን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦችን የአፋ አዋርድ ልዩ ተሸላሚ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የአፋ ሽልማት (AFFA Award) እና የፋሽን ሾው የፊታችን ቅዳሜ ሕዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም በዲሊኦፖል ሆቴል እንደሚካሄድ ኮሌጁ የምስረታ በዓሉን አከባበር አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።

በመግለጫው ላይ ከአዋርዱ በተጨማሪ ኔክስት ፋሽን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እንደሚያከበር የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ያሰለጠናቸውን ከ350 በላይ ተማሪዎችም በዕለቱ እንደሚያስመርቅ ተነግሯል።

በመድረኩ ላይ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠሩ የተለያዩ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች የሚሸለሙ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ ጆኒ ቪዲዮ አንዱ እንደሆ ተጠቅሷል።

Post image

በተጨማሪም በቆዳ ምርት ዘርፍ ላይ በመስራትና በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ሳምራ ሌዘር ሌላኛው የኦፋ አዋርድ ሲሆን፤ የኔክስት ዲዛይን የብዙ ዓመት ደንበኛ ለሆነችው አርቲስት ሀመልማል አባተም ልዩ ሽልማት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

እንዲሁም በአዋርዱ አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ ሌላኛዋ ተሸላሚ ስትሆን፤ በሜክአፕ ዘርፍም ሽልማት ይካሄዳል ተብሏል።

Post image

ኮሌጁ እስካሁን በመደበኛው የሥልጠና ፕሮግራም ከ5 ሺሕ 200 በላይ ዲዛይነሮችን በፋሽን ዲዛይን አሰልጥኖ አስመርቋል።

ኮሌጁ ከዓለም አቀፍ ተመሳሳይ የማሰልጠኛ ተቋሞች ጋር ባፈራው የስራ ግንኙነት እና ከህንድ ኤምባሲ ጋር ባፈራው መልካም የስራ ግንኙነት መሰረት 42 ዲዛይነሮችን በህንድ ሀገር ሙሉ የነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እና ስልጠናቸውን ተከታታትለው በመመለስ ለኢንዱስትሪውና ለሀገራቸው ትልቅ አስተዋፆ ማበርከት እንዲችሉ አድርጓል።

የኮሌጁ መስራች የሆነችው ወ/ሮ ሳራ መሐመድ በሃያ ዓመት የሥራ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ሽልማቶችን ማግኘቷን ገልጻለች።

Post image

ኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ ከ1 ሺሕ 500 በላይ የሳዑዲ ተመላሾችን በነፃ አስተምሮ ሥራ በማስቀጠር ማሕበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ