ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ ከ5 ሺሕ በላይ ሀገር በቀል የረድኤት ድርጅቶች መካከል፤ ግጭትን ያገናዘበ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የተቀረጸ ፖሊሲ ያላቸው ተቋማት 6 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ እንሆኑ በጥናት መረጋገጡ ተገልጿል።
ጥናቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ እና በአፋር ክልሎች ላይ አተኩሮ የተሰራ ነው ተብሏል።
'ቱፒ ኮንሰልቲንግ' በተባለ ተቋም የተካሄደውና በኢትዮጵያ ግጭትን ታሳቢ ያደረገ እርዳታ አካሄድን በጥልቀት እንደመረመረ የተነገረለት ጥናት እንዳረጋገጠው፤ በተለይም ተቀማጭነታቸው እና የተመሠረቱት ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ የረድኤት ድርጅቶች ስለ ግጭት አገናዛቢ ሰብአዊ እርዳታ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው።
በጥናቱ የተሳተፉት ቀዲዳ ሶንቶ (ዶ/ር) "የእርዳታ ድርጅቶች ራሳቸውን ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ አድርገው ቢያስቡም፤ በሚሰጡት እርዳታ ሲገመገሙ ግን ገለልተኛ ያለመሆን ዕድል እንዳላቸው ፍንጭ ይሰጣል" ብለዋል።
በተጨማሪም ተቋማቱ ስለ ግጭት አገናዛቢ ሰብዓዊ እርዳታ ግንዛቤው ቢኖራቸው እንኳን፤ የመተግበር አቅም፣ የበጀት እና የጊዜ እጥረት ይፈትናቸዋል ተብሏል።
ዶክተር ቀዲዳ በማብራሪያቸው፤ ግጭትን ያገናዘበ ድጋፍን በተመለከተ የግል ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ተቋማትም በቂ መረዳት እንደሌላቸው አንስተዋል።
የተስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት ተቋማቱ ስልጠና መስጠት እና በጀት መመደብ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የሰብዓዊ እርዳታዎች ከፖለቲካ ፍላጎት አንጻር የሚከወኑበት ጊዜ እንዳለ ያስታወሱት በጥናቱ የተሳተፉት ባለሙያ፤ በእርዳታ ሰጪ የረድኤት ድርጅቶች እና በክልል ወይም በዞን አመራሮች መካከል የሚደረገው የድጋፍ ክፍፍል እና "ለማን ይሰጥ" የሚለው ውሳኔ ልዩነት ሲፈጥርና ችግር ሲያስከትል እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።
በጥናቱ ከተሳተፉት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ገመቺስ ጥሩነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ እርዳታ ለግጭት መባባስ ወይም ለሰላም መስፈን የራሱ የማይናቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
"የረድኤት ድርጅቶች የሰብዓዊነት ድጋፍ ግጭትን ባገናዘበ መልኩ ለመምራት የሚያስችል ፖሊሲ የላቸውም" ያሉት ዶክተር ገመቺስ፤ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ድርጅቶች በጽሑፍ የሰፈረ ፖሊሲ የሌላቸው ሲሆን 63 በመቶ የሚሆኑት ፖሊሲው እንዳላቸው ቢገልጹም በተገቢው ሁኔታ ወደ ተግባር እንዳልቀየሩት ተናግረዋል።
መንግሥታዊ ከሆኑት እና ካልሆኑት የረድኤት ድርጅቶች በተጨማሪ፤ መንግሥት ወደ ሀገር የሚገባው ድጋፍና እርዳታ ግጭትን እንዳያባብስና ለሰላም አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚቆጣጠርበት ፖሊሲ ያስፈልገዋል ተብሏል።
እርዳታ እና ድጋፎች ለሰላም አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ከማኅበረሰቡ፣ ከደጋፊ አካላት እና ድጋፉን ከሚያሰራጩት ወገኖች ብዙ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።
እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ እና የመን ያሉ በግጭት ውስጥ የቆዩ ሀገራት ግጭትን ያገናዘበ እርዳታን በተመለከተ የተሻለ ተሞክሮ እና አሠራር አላቸው ተብሏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ ግጭትን ያገናዘበ የድጋፍ ፖሊሲ ያላቸው ሀገር በቀል የረድኤት ድርጅቶች 6 በመቶ ብቻ እንደሆኑ አንድ ጥናት አረጋገጠ