ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ልማት ድጋፍ ፕሮጀክት ሥር ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማስፋት፣ የኢትዮጵያ የዋስትና ልውውጦችና የምርት አቅርቦቶችን ለማብዛት እና አቅምን ለማጠናከር የሚውል የ400 ሺሕ ዶላር ድጋፍ ፈቅዷል።
ድጋፉ በአፍሪካ ልማት ባንክ ሥር ከሚተዳደረው የካፒታል ገበያ ልማት ትረስት ፈንድ (ሲ.ኤም.ዲ.ኤፍ.ኤፍ) በኩል ከብዙ ለጋሾች የሚገኝ ይሆናል ተብሏል።
የገንዘብ ድጋፉ የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ባለስልጣን መረጃን ለባለሀብቶች፣ ለባለ አክሲዮኖች እና ለሌሎች የገበያ ተዋናዮች ወቅታዊና ትክክለኛ በሆነ መልኩ ለማሰራጨት እንደሚውል የተገለጸ ሲሆን፤ በገበያ ላይ የውሳኔ አሰጣጥ እና ፍትሃዊ የዋጋ ግኝትን ለማሻሻል የሕዝብ ይፋዊ መድረክ እንዲቋቋም ያግዛል ተብሏል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ባለስልጣን አቅርቦቱን በማስፋፋት የምንዛሪ ፈንዶችን፣ “ሱኩክ” የተሰኘው ከወለድ ነጻ የቦንድ ሽያጭ አገልግሎት እና አረንጓዴ ቦንዶችን አገልግሎት ለማሳደግ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልኩ "በዚህ ወሳኝ ፕሮጀክት ላይ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የካፒታል ገበያ ልማት ትረስት ፈንድ ጋር በመተባበራችን ኩራት ይሰማናል" ያሉ ሲሆን፤ "ድጋፉ ንቁ እና ጠንካራ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ እንዲኖር የጋራ ራዕያችንን ያንፀባርቃል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለባለሥልጣኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የአቅም ግንባታ እና የምርት ብዝሃነት ለማስደግ የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ፤ ለአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ "የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጠቃሚ ይሆናል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ያለውን የምርትና አገልግሎት አቅም ለማጎልበት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር አጋርነት በመፍጠሩ ደስተኛ ነን" ብለዋል።
"ትብብሩ የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳር መሠረት በመጣል የተገኘውን ከፍተኛ እድገት ከግምት ውስጥ ያስገባና ወቅታዊ ነው" ያሉም ሲሆን፤ ለድጋፍ አድራጊዎች እና ለባለሀብቶች ተጨባጭ ተፅእኖ በሚያመጡ ትብብሮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉበት ጊዜው አሁን መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንሺያል ዘርፍ ልማት ዳይሬክተር አህመድ አትቱት በበኩላቸው፤ "የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ልማት ድጋፍ ፕሮጀክት፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በብቃት ካፒታልን ለመሳብ እና ለማሰማራት የሚያስችል የፋይናንስ ማዕከል ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ ያለውን ራዕይ የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡
ባንኩ አሁን ያደረገው የካፒታል ገበያ ልማት ድጋፍ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ድጋፉ ከምዕራብ አፍሪካ ውጭ አህጉራዊ የካፒታል ገበያ ልማትን ማስፋፋት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
የፕሮጀክቱ ሰፊ ዓላማ ለመንግሥት እና ለግሉ ዘርፍ በካፒታል ገበያ የረጅም ጊዜ ፋይናንስ አቅርቦትን በማሻሻል የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ እና ኢኮኖሚ ለማስፋፋት አስተዋፅኦ ማድረግ ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡
የካፒታል ገበያ ልማት ትረስት ፈንድ የአፍሪካ የካፒታል ገበያ ተቋማትን ለመደገፍና ለማስፋፋት እ.ኤ.አ በ2019 የተቋቋመ ሲሆን፤ ከኔዘርላንድስ የውጭ ንግድ እና ልማት ትብብር ሚኒስቴር፣ ከሉክሰምበርግ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ከስዊድን አለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ (SIDA) ለጋሾች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮጀክቱ ይተገበራል።
ፈንዱ በምዕራብ አፍሪካ በሙከራ ፕሮጀክቶች የጀመረ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 2025 ድረስ በ16 አገሮች ውስጥ የ6 ሚሊዮን ዶላር ገቢር ማሳያ አለው።
ኢትዮጵያ በዚህ የካፒታል ገበያ ልማት ትረስት ፈንድ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆነች የመጀመሪያዋ ምስራቅ አፍሪካዊ ሀገር እንደሆነችም አሐዱ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ