ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 41ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ መርምሮ በማጽደቅ፤ በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት አመት ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር ተወያይቷል።
የ2018 በጀት ዓመትን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ ወንድወሰን አድማሱ በ2017 በጀት ዓመት ከጠቅላላ በጀቱ ለትምህርት፣ ለመንገድ፣ ለጤና ተመድቦ የነበረው 34 በመቶ ሲሆን፤ በ2018 ረቂቅ በጀት ላይ 25 ነጥብ 5 በመቶ መመደቡን ገልጸዋል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት 35 በመቶ ያነሰ መሆኑን አስረድተዋል።
"ይህ ደግሞ ለድህነት ተኮር ሴክተር በምን ያህል መሸፈን የሚችል ይሆናል?" ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። አክለው የ2018 በጀት ዓመት ከባለፈው ዓመት 34 በመቶ ብልጫ ያለው ቢሆንም፤ ለክልሎች የተበጀተው በጀት ግን ከተደረገው ጭማሪ አንጻር ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
ሌላው የምክር ቤት አባል የሆኑት ተስፋዬ ባንጉ በበኩላቸው፤ ለክልሎች የሚደረገው በጀት ወቅቱን ጠብቆ የማይደርስ በመሆኑ የሚሰሩ ሥራዎች ተግባራዊነት ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይም ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የምክር ቤት አባሉ አቶ ባጤማ ፈቃዱ "በገጠር የሚገኙ የሴፍቲ ኔት ተጠቃሚዎች እራሳቸውን በመቻል እና ከፍ በማለት ከሴፍቲኔት ተጠቃሚነት መላቀቅ እየቻሉ ቢሆንም፤ በከተማ ያለው የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ግን የመቀነስ እና የመላቀቅ ነገር የማይታይበት በመሆኑ ተጠቃሚዎችን መፈተሽና ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጥ የሚገባ ነው" ብለዋል።
"ለመሰረታዊ የልማት በጀቶች በሚያስፈልገው መጠን ጨምሯል" ሲሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፤ "የክልሎች የጋራ ገቢ መጨመር እና የፕሮፐርቲ ታክስ ለክልሎች የተሻለ ገቢን የሚፈጥር መሆኑን ከግንዛቤ ያስገባ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም "ክልሎች የገቢ መጠናቸውን ለመጨመር ምርታማነትን ማሳደግ እና ኢንቨስትመንትን መሳብ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።
አክለውም "የሪፎርም አላማ ገቢን መጨመር ነው" ያሉ ሲሆን፤ መንግሥት የወጪ ፍላጎቱን በገቢ አቅሙ የሚሸፍንበት አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ "የተቀመጠውን የታክስ እቅድም መሰብሰብ የሚችል መሆኑ በዘንድሮው ዓመት የታየ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ ዘሀራ ቢፍቱ የዴሞክራሲ ተቋማት በጀትን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ "እነዚህ ተቋማት የፋይናንስ ነጻነትን የሚፈልጉ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመንግሥት የሚደረግለት በጀት በተለያዩ አካባቢዎች የአካባቢያዊ ምርጫ እንዳያደር ያገደ መሆኑና የአካባቢያዊ ምርጫ ሳይደረግ 10 ዓመት ማለፉን አንስተዋል።
የምክር ቤት አባሏ በ"ቀጣዩ ዓመት የሚደረገው ምርጫን አስመልክቶ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን ታቅዷል?" ሲሉ ጠይቀዋል።
እንዲሁም የእንባ ጠባቂ ተቋም በጀት በጣም አነስተኛ መሆኑን ገለጸው፤ "የሚመደብለት በጀት 80 በመቶውን ለቢሮ ኪራይ የሚክፍልና የቢሮ መቀያየር ችግር ያለበት ነው" ብለዋል።
"ይኸው የበጀት እጥረትም የሚያስፈልገው የሰው ሃይል 1 ሺሕ 545 ሲሆን፤ ቅንጫፎች ላይ ያሉትን ጨምሮ 300 ብቻ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የበጀት ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢያቀርብም ውስን በጀት ብቻ እንደሚቀቅለት የገለጹ ሲሆን፤ ሥራዎችን ለመስራት እና ክትትል ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር የሚሰራበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።
"ይህ ደግሞ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ያደርገዋል" ብለዋል።
ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የዴሞክራሲ ተቋማት በጀትን በተመለከተ ውይይት ተደርጎበት መወሰኑን ገልጸው፤ "ለሁሉም ተቋማት ያለው አሰራር ተመሳሳይ በመሆኑ ከግንዛቤ ሊገባ ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ ዘሀራ ቢፍቱ የዴሞክራሲ ተቋማት ትኩረት በማድረግ የፋይናንስ ነጻነትን በመስጠት ገለልተኛና ነጻ እንዲሁም ከሀገራዊ አቅም ጋር አጣጥሞ መመደብ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
እንዲሁም ከአስፈጻሚ አካላት ተጽዕኖ ነጻ ሆነው በተልዕኳቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተውበታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ