ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በስፔን ሲቪያ በመካሄድ ላይ በሚገኘው አራተኛው ዓለም ዓቀፍ የዘላቂ ልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ ጎን ለጎን በተዘጋጀው ልዩ ስብሰባ ላይ፤ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አስተዳደርን ለማሻሻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርባለች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ እንደገለጹት፤ "የሲቪያ ቁርጠኝነት" የእዳ ጫና፣ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ እና በዓለም ላይ እየሰፋ የመጣውን የሀገራት የእድገት ልዩነት ለመፍታት ልዩ እድል የፈጠረ ነው።

Post image

በቡድን 77 (G-77)፣ በአፍሪካ ቡድን፣ በልማት ታዳጊ አገራት (LDCs) እና ማሻሻያ ፈላጊ በሆኑ በሰሜኑ አጋሮች መካከል የታየውን ያልተለመደ የፖለቲካ ፍላጎት ትብብር ያነሱት ቋሚ መልዕክተኛው፤ ይህ አንድነት ወደ ተጨባጭ እርምጃ እንዲለወጥ አሳስበዋል።

አክለውም፤ ሦስት ቁልፍ ዕድሎችን ለይተው አስቀምጠዋል፡፡ እነሱም የተዋሃደ ማሻሻያ ፣ ጠንካራ የግሎባል ሳውዝ አመራር እና የማሻሻያ ጥምረቶች ፍጥነት መሆናቸውን አንስተዋል።

ለውጡን ለማስቀጠል የጊዜ ገደቦች፣ ተጠያቂነት እና የተባበሩት መንግሥታት የሚመራ ቋሚ ሂደት እንዲኖር ጥሪ ያቀረቡም ሲሆን፤ እርምጃ አለመውሰድ ዓለም አቀፍ መዘዝ እንደሚያስከትልም ማስጠንቀቃቸውን አሐዱ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

Post image

በስፔን ሲቪያ ትናንት ሰኔ 24 ቀን ተጀምሮ እስከ ነገ ሰኔ 26 ቀን 2017 ድረስ በሚቆየው በዚህ አራተኛው ዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ ላይ በግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ የልዑክ ቡድን በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት ያስመዘገበችውን ውጤት በኮንፍረንሱ ላይ በተሞክሮነት ያጋሩ ሲሆን፤ በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርጋቸውን ሌሎች ጥረቶች እንደ ልምድ አቅርበዋል።

እንዲሁም ከ10 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ መካሄዱን አስታውሰው፤ ነገር ግን በኮንፍረንሱ የጸደቀው የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ-ግብር የአተገባበር ተግዳሮት እንደገጠመው አስታውቀዋል፡፡

Post image

በዚህም ዘላቂ የልማት ግቦችን ለመተግበር ከሚያስፈልገው ፋይናንስ ውስጥ የ4 ትሪሊዮን ዶላር እጥረት መግጠሙን በማንሳት፤ "የሲቪያ ስምምነት ይህንን ተግዳሮት የሚሻገር መሆን ይገባዋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መልዕክት ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት፣ ፍትሃዊ እና አካታች የፋይናንስ ስርዓት እንዲኖር ከታዳጊ ሀገራት እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት የሚያስተጋባ ስለመሆኑም በኮንፍረንሱ ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ