ጥቅምት 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በመጪዎቹ 10 ዓመታት ውስጥ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን በዓለም ላይ ከሚገኙ 10 ምርጥ የጦር ሙዚየሞች ውስጥ አንዱ እንዲሆን ለማድረግ እቅድ ተይዞ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ፤ የሙዚየሙ አስተዳደር ለአሐዱ አስታውቋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ትላልቅ ሙዚየሞችን የገነቡ ሀገራት ቢኖሩም፤ የአድዋ ድልን ከፍታ የሚሰተካከል ድል ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት የሉም ሲሉ ለአሐዱ የገለጹት የሙዚየሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግሩም ግርማ ናቸው።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየሙም ከኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን ባሻገር የመላው ነፃነት ናፋቂ ሕዝብ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

ከታሪኩ ትልቅነት አንፃር ላቅ ያለ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንን ለማሳካት ብቁ የሰው ሀይል እና የታሪክ ግንባታው ላይ በሰፊው እንደሚሰራ ገልጸዋል።

Post image

በተጨማሪም ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማሟላት እንዲሁም የሙዚየሙን ስርዓት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ስርዓት እንዲሆን የማድረግና የማስታወቂያ ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

ከዚህም ሌላ ቋሚ ኢግዚብሽን የሚታይበት ሙዚየሙን የበለጠ ለጎብኛዎች ሳቢና ማራኪ በሚሆን መልኩ ለማስተካከል የጎደሉ ሥራዎችን የማሟላት ሂደት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዚህም በእርግጠኝነት በዓለም ላይ የሚገኙ ምርጥ 10 የጦር ሙዚየሞች ካሉበት ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

"ይህንን ራዕይ ማሳካት ግዴታችን ነው" ሲሉ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በየደረጃው ከመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራበት አስታውቀዋል።

Post image

የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየሙ ከተከፈተ ገና አጭር ጊዜው ቢሆንም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችን መሳብ የቻለ እና ለተለያዩ ጉባኤዎችና ለመዝናኛ ዝግጅቶች ተመራጭ እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ነግ ግን የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን አብዛኛው ሰው ያለው 'ባለስልጣናት ብቻ የሚገቡበት ነው' የሚል የተሳሳተ አረዳድ ለአገልግሎቱ ተግዳሮት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ግሩም ግርማ ለአሐዱ ገልጸዋል።

ሙዚየሙ በዋናነት ከአድዋ ድል ጋር በተገናኘ ያለውን ታሪክ ለሀገራዊ አንድነት ገፅታና ለመግባባት ጠቃሚ እንዲሆን ታስቦ መሰራቱን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት አንስቶም እስካሁን ባለው ጊዜ እንደ ተግዳሮት የሚነሳው በሙዚየሙ ላይ ሰዎች ያላቸው አረዳድ መሆኑን ተናግረዋል።

ብዙ ሰዎች 'ሙዚየሙ ባለስልጣናት የሚገቡበት ብቻ እንጂ ለሌሎች ጎብኚዎች የሚፈቀድ አይደለም' ብለው እንደሚያስቡ አንስተዋል።

Post image

በዚህ ሂደት ግን አንዳንዶች በአጋጣሚ መጥተው በማየት ለሁሉም ክፍት መሆኑን ሲረዱ ደግሞ ግንዛቤያቸው የተሳሳተ እንደሆነ ይነግሩናል ሲሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህንን አመለካከት ለመፍታት በተለያዩ አማራጮች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚሰራበት ጠቁመዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በተያዘው በጀት አመት ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

ይህም ከሙዚየሙ ጉብኝት እንዲሁም ከፓርኪንግ፣ ከሲኒማ ቤት እና ከተለያዩ የንግድ አገልግሎቶች እና ሌሎችም የሚገኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ