ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በግብር አሰባሰቡ ሂደት የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን፣ ሌብነትንና በሠራተኞችና በግብር ከፋዮች መካከል የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችል ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበት የቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን ይፋ አድርጓል።
ይህንን የተገለጸው የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ፤ በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበት የቁጥጥር ባለሙያዎች በአካል ላይ የሚገጠም ካሜራ ወይም ቦዲ ዎርን ካሜራ ፕሮጀክትን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ማስገባት ተችሏል።
ይህ አዲስ የካሜራ ቴክኖሎጂ በግብር ከፋዩ እና በሠራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታትና ብልሹ አሠራሮችን በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሏል።
አቶ ቢኒያም እንዳብራሩት፤ የካሜራ ቴክኖሎጂው በተለይ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያው ከግብር ከፋዩ ጋር የሚያደርገውን ንግግርና እንቅስቃሴ በምስልና በድምጽ የሚቀዳ የቴክኖሎጂ አሠራር ነው። ይህ ስርዓት ለሚነሱ ማንኛውም ቅሬታዎች ተጨባጭ መረጃ በመስጠት መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል።

ቢሮው የከተማ አስተዳደሩ በመደበው በጀት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት (ኢንሳ) ጋር በመቀናጀት ሕግ ማስከበርና ቁጥጥር ሥራዎችን እንደሚሠራ አቶ ቢኒያም አስታውቀዋል።
"ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርጉት ባለሙያዎችም የሠለጠኑ ናቸው" የተባለ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት በከተማ ደረጃ 350 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ ኃላፊው አብራርተዋል።
ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የገቢ መሠረቶችን ማስፋት፣ የሌብነትና ብልሹ አሠራሮችን መከላከል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን ማጎልበት፣ ለመሳሰሉት ዓላማዎች የሚረዱ አዳዲስ አሠራሮችን፣ አደረጃጀቶችን በማጥናት እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ወደ ተግባር መሸጋገሩን ቢሮው ገልጿል።

ከታክስ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ቅሬታዎች ችግሮች በተሻለ መልኩ እየተፈቱ እንደሚገኙ የተገለጸም ሲሆን፤ ማናቸውም ከግብር ጋር በተያያዘ "ቅሬታ አልተፈታም" ለሚሉ አካላት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሚመራ ቅሬታ የሚፈታ ቡድን በመቋቋሙ ችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋል ተብሏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ