ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለመደገፍ የግሉ ዘርፉ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ መሳተፍ እንደሚጠበቅበት የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍሥሐጽዮን አሳሰቡ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ያሉት 2ኛው ቀጠናዊ የካፒታል ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የወደፊት ተስፋን ለዜጎቿ ለመገንባት የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዳላት ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴታው እንዳሉት፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ከመንግሥት ባሻገር የግል ዘርፉን የገንዘብ ድጋፍ ይጠይቃል።

የግል ዘርፉ ከካፒታል ገበያው ጋር በመተባበር በኃይል፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በደን ልማት፣ በኢንዱስትሪ እንዲሁም ዘላቂነት ባለው የከተማ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ የአረንጓዴ ኢኮኖሚውን መሠረት ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

ካፒታል ገበያው ፋይናንስን በማሰባሰብ ከአየር ንብረት ጋር የተጣጣሙ የፍትሐዊነት ኢንቨስትመንቶችን፣ የካርቦን ገበያ መሣሪያዎችን፣ የፋይናንስ መዋቅሮችን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል የመሠረተ ልማት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችል ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

አክለውም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የልማት ስትራቴጂ ዋና ምሰሶ መሆኑን አንስተው፤ ይህንን ሂደት ለማፋጠን ደግሞ የካፒታል ገበያ ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን አብራርተዋል።

መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን በማዘመን እና የአየር ንብረት ዘላቂነትን ማዕከል በማድረግ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ በርካታ መሠረታዊ የሆኑ የአየር ንብረት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማውጣት ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች።

ይህ ሥራ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ፋይናንስን በስፋት እንድታንቀሳቅስ፣ የግል ኢንቨስትመንትን እንድትስብ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉትን ዓለም አቀፍ ዕድሎች እንድትጠቀም ያስችላታል ተብሏል።

በዛሬው ዕለት ሁለተኛ ቀኑን በመያዝ በመካሄድ ላይ ያለው 2ኛው ዓቀጠናዊ የካፒታል ጉባኤም የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን ለመደገፍ እንደሚያግዝ ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ