ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዘጋጀውን የ"ጋስትሮኖሚ" ወይም የምግብ አዘገጃጀት ጥበብን፣ የምግብ ባህልን እና ሳይንስን የሚያሳይ የምግብ ፌስቲቫል ለማካሄድ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ይፋ አድርጓል።

ፌስቲቫሉ ጥር 9 እና 10 ቀን እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን የበለጸገ የምግብ ባሕል ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎለታል።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ፤ ፌስቲቫሉ በጥር ወር እንዲካሄድ የተመረጠበት ምክንያት ጥር ወር ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም፤ "ፌስቲቫሉ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት እና በቱሪዝም ዘርፍ የምግብ ሥርዓቱን ለማሳወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል" ብለዋል።

በፌስቲቫሉ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ የባሕላዊ ምግቦችን ያካተተ ውድድር እንደሚካሄድና አሸናፊዎች እንደሚሸለሙ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ ሆቴሎች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንና በሀገሪቱ የሚገኙ ባህላዊ ምግቦች ለውድድር እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

ፌስቲቫሉ በሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምግቦች በመኖራቸው፤ በቱሪዝሙ ዘርፍ የሀገሪቱን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሳወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

Post image

ፌስቲቫሉን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ከጎልደን ግሩፕ ሆስፒታሊቲ ጋር ለመሥራት ስምምነት ማድረጉ ታውቋል። በተጨማሪም ፌስቲቫሉ በየዓመቱ እንዲካሄድ እቅድ ተይዟል ተብሏል።


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ