ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በከተማዋ የሚገኙ ወንዞችን ሙሉ ለሙሉ ከብክለት የፀዱ ለማድረግ የሚሰራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸ ሲሆን፤ የቆሻሻ ፍሳሻቸውን ወደ ወንዝ ለመልቀቀ ከቱቦ ጋር ያገናኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከ50 ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው አስታውቋል፡፡

የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲዳ ድሪባ ከአሐዱ ሬዲዮ ከቅዳሜ ገበያ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የውሀ፣ የድምፅ የአየርና የመሳሰሉት የተለያዩ የአካባቢ ብክለቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ብክለት ለመከላከል ደግሞ አዳዲስ ሕጎችን ማውጣትና የወጡትን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ ዙሪያ ለአብነትም ደንብ ቁጥር 180/2017 የአዲስ አበባ ወንዞች ልማትና ብክለት መከላከል ደንብ መውጣቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህ ደንብ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግም ቁጥጥር እንደሚደረግበት አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ወንዝ ዳር ያሉ በግለሰብም ሆነ በተቋም ወይም በፋብሪካዎች ደረጃ ወንዞችን እንደ ቆሻሻ ቦይ የመጠቀም ሕገ-ወጥ ድርጊት መኖሩን አንስተዋል።

በዚህ ደንብ መሠረት ግን ፍሳሻቸውን ቆሻሻቸውን ወደ ወንዙ ለመልቀቀ ከቱቦ ጋር ያገናኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከ50 ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተናግረዋል።

በዚህ አግባብ የወንዞችን ብክለት ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ያነሱ ሲሆን፤ አሁንም ቀሪ ሥራዎች በመኖራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ የወንዞች ብክለትን ከመከላከል ባሻገር ችግኞችን የመትከል፣ አካባቢን የማፅዳትና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙ የድንጋይ ማዕድናትን በማውጣት ለመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲውሉ ይደረጋል ብለዋል።

አሐዱ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ተረፈ ምርታቸውን ወንዝ ውስጥ እንደሚለቁ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በጥናት ማረጋገጡን መዘገቡ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ