ጥቅምት 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በመንግሥትም ይሁን በግለሰብ ደረጃ የአሳ ምርትን ወደ ውጭ የሚትልክበት የአሰራር ስርዓት እስካሁን እንደሌላት ግብርና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ጌታቸው መኮንን (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአሳ ምርት አቅሟ እያደገ ቢመጣም የአሣ ምርትን ወደ ውጪ ሀገራት የምትልክበት የአሰራር ስርዓት እስካሁን አለመዘርጋቱን ተናግረዋል።

Post image

ምክንያቱን ሲያስቀምጡም፤ እንደ ሀገር የአሳ ምርት ጥራት ላይ እውቅና የሚያሰጥ ሥራ አለመሰራቱ እና የተወዳዳሪነት መስፈርትን አለማሟላት ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገርም የአሳ ምርት የሚቀበሉ ሀገራትን ፍላጎት ጠንቅቆ የመረዳት አቅም ማነስ እንዲሁም የውጭ ሀገራት እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ የዓሳ ምርት ፍላጎት አለማሳየታቸው ለችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ከፍተኛ አማካሪው ገልጸዋል።

በዚህም ከዓለም 10ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ግዙፍ ፕሮጀክት የሆነው የሕዳሴው ግድብን ጨምሮ፤ የተለያዩ ሃይቆች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የምታመርተውን ከፍተኛ የአሳ ምርት ጥራት ለማሳደግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ዘርፉም ሀገራዊ ምጣኔ ሃብታዊ እድገትን ለማሳለጥ በሚያስችል መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

Post image

በኢትዮጵያ ባሉ የውሃ ሀብቶች ውስጥ ከ200 በላይ የአሳ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 45 የሚሆኑት በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የአሳ ዝርያዎች ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በመጠቀም ከ255 ሺሕ ቶን በላይ ምርት በዓመት የምታገኝ ሲሆን፤ 530 ሺሕ ቶን አሳ ማምረት እንደምትችል በጥናት መረጋገጡን ሚኒስቴሩ ለአሐዱ መግለጹ ይታወሳል።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ