ጥቅምት 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ስፍራዎች የውጭ ሀገር ዜጎች በተከለከሉ ስፍራዎች ላይ ሲጋራ እያጨሱ እንደሆነ እና በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ተቋማት በተለይም ሆቴሎች የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ሲጋራ እንዲያጨሱ ፍቃድ እንደሚሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአሐዱ አሰምተዋል።
ነዋሪዎቹ ተቋማቱ የተለየ ገቢ ለማግኘት በሚል ድርጊቱ እንዲፈፀም እንደሚፈቅዱ ጠቁመው፤ በዚህም ምክንያት ለጤና እክል ተጋልጠናል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የንግድ ቤቶቹ የትንባሆ ምርት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን መመርያ እየጣሱ ይገኛሉ ሲሉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

አሐዱም፤ የነዋሪዎችን ቅሬታ በመያዝ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንን ጠይቋል።
በባለሥልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው ለአሐዱ በሰጡት ምላሽ፤ ለውጭ ዜጋ ተብሎ ሕጉ የሚጣስበት ምክንያት የለም። ተቋማት ይህንን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
ይህንን መመርያ ጥሰው በሚገኙ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ነው ዳይሬክተሩ ያረጋገጡት፡፡
ገቢ ለማግኘት በሚል መመርያውን ተግባራዊ የማያደርጉ የንግድ ተቋማት እና ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸዉ ተቆጥበው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ መሰል ተግባር በሚያስፈፅሙ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በንግድ ተቋማት፣ በሆቴል ቤቶች እና ሰው በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ላይ የውጭ ዜጋን ሲጋራ የሚያስጨሱ ተቋማት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ትምባሆ በጤና፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚና በአካባቢ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምግብ መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ቢወጣም በአግባቡ ባለመተግበሩ፣ የኢትዮጵያን 70 በመቶ የሚወክሉትን ወጣቶች ለአደጋ መዳረጉን ጤና ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ